በትግራይ ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች እና ንጹሑሃን ዜጎች መገደላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ ግጭት ከጠፋው ሕይወት በተጨማሪ ባለፉት 8 ወራት ብቻ የሠራዊቱን ወጪ ሳይጨምር የፌደራሉ መንግሥት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማደረጉን ገልጸዋል።

በትግራዩ ጦርነት በሰው እና በሃብት ላይ የደረሰን ጉዳት በተመለከተ በፌደራሉ መንግሥት ሲነገር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ነገር ግን አምባሳደር ሬድዋን በጦርነቱ በፌደራሉ መንግሥትም ይሁን በህወሓት ኃይሎች በኩል በሰው ላይ የደረሰ የሞት ቁጥርን አልጠቀሱም።

ጦሩ መቀለን የለቀቀው በፖለቲካዊ ምክንያት ነው

አምሳደር ሬድዋን ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ በሰጡት መግለጫቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀለን የለቀቀው በፖለቲካዊ ውሳኔ እንጂ በወታደራዊ ምክንያት አይደለም ብለዋል።

የህወሓት ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው በዚህ መግለጫ አምባሳደር ሬድዋን ጦሩ ትዕዛዝ ቢሰጠው በሳምንታት ውስጥ ከተማዋን መልሶ መቆጣጠር ይችላልሲሉ ተናግረዋል።

የህወሓት ኃይሎች በወታደራዊ ድል መዲናዋን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን የፌደራሉ ጦር ስፍራውን ለቆ በመውጣቱ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ግጭቱ እንዲቆም እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ በማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ ጫና ማድረግ የለበትም ብለዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ መንግሥት ያወጀውን የተኩስ አቁም ተከትሎ የእርሻ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው የክረምት ወራት ግጭት አይኖርም።

line

ከሁለት ቀናት በፊት፣ ሰኞ ሰኔ 21/2013 .ም፣ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ በአስቸኳይ ተፈጻሚ የሚሆን የተኩስ አቁም አውጆ የክልሉን መዲና ለቅቆ መውጣቱ ይታወሳል።

የፌደራሉ ሠራዊት መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የህውሓት አማጺያን ዋና መዲናዋን መቀለን ጨምሮ በርካታ የክልሉን ስፍራዎች እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ።

አማፂያኑ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የምትገኘው የሽረ ከተማን እንደተቆጣጠሩ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች አስታውቀዋል።

ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በበኩሉ አማፂያኑ በአሁኑ ወቅት የክልሉን አብላጫ ክፍል መቆጣጠራቸውን አስታውቋል።

የተኩስ አቁም የሚበረታታ እርምጃ ነው

የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም ያወጀው እና መቀለን ለቅቆ የወጣው ግጭቱ እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚል ምክንያት ስለመሆኑ በመንግሥት ተገልጿል።

ይህን የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ጥሪን ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ግጭቱን ለማስቆም አወንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

አምስት በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮች፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአፍሪካ ሕብረት የፌደራሉ መንግሥቱ ያወጀው ተኩስ አቁም በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት እንዲከበር ጥሪ ሲያቀርቡ፤ ቻይና እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ውሳኔን ተገቢ እርምጃ ሲሉ አድንቀዋል።

ይሁን እንጂ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የህወሓት ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ የተኩስ አቁሙ ጥሪው ቀልድነው ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ወደ አማራ ክልል መሄድ ካለብን እንሄዳለን፤ ወደ ኤርትራ መዝመት ካለብን እናደርገዋለንሲሉ ተናግረዋል።

ጌታቸው ረዳ ዋና ዓላማችን የጠላትን የመዋጋት አቅም ማዳከም ነውያሉ ሲሆን፤ ከኤርትራ፣ ከአማራ ወይም ከአዲስ አበባ በኩል ያሉ ጠላቶች የሕዝባችን የደኅንነት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብንብለዋል።

ቢቢሲ