2 ሀምሌ 2021

የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ በውይይት ለመፍታት ዕቅድ እንዳለው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ሚንስትሩ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ማኅብረሰብ አባላት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም የዝግ ስብሰባ እያካሄዱ ይገኛሉ።
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሕጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ችግሩን ለመፍታት ፍቃደኛ ከሆኑ ከታች ካሉ የህወሓት አባላት፣ ከሲቪል ማኅብረሰቡ እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ለመወያየት እቅድ አለው ሲሉ ተናግረዋል።
“ድጋፋችሁን እንፈልጋለን፤ እንድትረዱን እና ወዳጅነታችሁን እንሻለን” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ለዲፕሎማቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን የህወሓት ቡድን ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት በሰላም ለፍታት ፍቃደኛ ሳይሆን ስለመቅረቱ እና ለተፈጠረው ጦርነት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
- ለኢትዮጵያ መንግሥት የተኩስ አቁም ውሳኔ አገራትና ዲፕሎማቶች የሰጡት ምላሽ
- የተናጠል ተኩስ አቁሙና ያልተመለሱ ጥያቄዎች
- የትግራይ ኃይሎች መቀለን ተቆጣጠሩ፤ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አወጀ
ከዚህ በተጨማሪም የህወሓት ቡድን ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥሪ በማድረግ ወጣቶች በጦርነቱ እንዲሳተፉ ማድረጉን እና በርካታ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
እንደ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ባንክ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የፌደራሉ መንግሥት ሲገነባ የህወሓት ኃይል ግን መሠረተ ልማቶቹን እያወደመ ነው ሲሉም ከሰዋል።
በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የባሉ ሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያጣራ ቡድን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አቶ ደመቀ አስታውሰው፤ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ የምርመራ ውጤቱ ሳይታወቅ የአንድ ወገን አመለካከተን ከመያዝ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ድጋፍ የሚሹ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳለው የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ መንግሥት “ረሃብን እንደ ጦርነት ተጠቅሞታል” የሚለው ክስ ሐሰት መሆኑን እና መንግሥት መሰል ተግባር የመፈጸም አንዳች ፍላጎት እንደሌለው ተናግረዋል።
መንግሥታቸው በአስቸኳይ ተፈጻሚ የሆነ የተኩስ አቁም ማወጁ የክልሉ ነዋሪዎች በክረምቱ ወራት በእርሻ ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ እና የከፋ ችግር እንዳይከሰት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቁን ተከትሎ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁ አስታውቆ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ እንደወጣና የተለያዩ አካባቢዎች በአማጺያን እጅ መግባታቸው ይታወሳል።