የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በትግራይ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደታሰሩና ለእንግልት መዳረጋቸው እንዳሳሰባቸው ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ በክልሉ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በግጭቱ ወቅት በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ከአንደኛው ወገን ጋር ትስስር አላችሁ ተብለው ለጥቃት፣ ለአፈና እና ለእስር መዳረጋቸውን የሚያመላክቱ ተዓማኒነት ያላቸው እና የተረጋገጡ መረጃዎች ደርሰውኛል ብለዋል።

ከፍተኛ ኮሚሽነሩ በተለይ በምሽት ሰዓት ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ ተብለው በሚጠሩ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች በስደተኞች ላይ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሽረ ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በመጥቀስ መቀለ ያሉ ባለስልጣናት ማብራሪያ እንዲሰጡ እና ለእስር የተዳረጉ ስደተኞና ጥገኝነት ጠያቂዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ትግራይ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ይዘው በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች አቅራቢያ ግጭት መከሰቱን ዘግቧል።

ኮሚሽነሩ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚቃጣው ጥቃት እና ስደተኞቹን ለፖለቲካ ጥቅም የማዋል ተግባር በአስቸኳይ ይቁም ሲሉ ጠይቀዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም ለኤርትራ ስደተኞች እና በትግራይ ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎች ደጋፍ ለማድረስ የሽረ እና መቀለ አየር ማረፊያዎች እንዲከፈቱ እንዲሁም መንገዶች ከፍት እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚኖሩ ይገመታል። ኤርትራውያኑ የአገራቸውን አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት እና አፋኝ አገዛዝን በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር ይሸሻሉ።

በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት ሲቀሰቀስ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከፍሎች የሸሹ ሲሆን አሁንም ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ስደተኞች የት እንዳሉ አይታወቅም።

የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች በስደተኞቹ ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶችን እንዲመረምሩ ኃላፊው ጠይቀዋል።

የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ላለፉት 8 ወራት ሲዋጉ ቆይተው ከሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።

ቢሆንም ግን ተኩስ አቁም ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጡት የትግራይ ኃይሎች በቅርቡ ባካሄዱት የመልሶ ማጥቃት የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው ስፍራዎች መካከል የሚገኙትን ኮረም እና አላማጣ ከተሞችን መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።

ቢቢሲ