ከ 8 ሰአት በፊት

ስደተኞች

በትግራይ በተነሳው ጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ኤርትራውያን ስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ በመጠለያ ጣቢያዎች ፀጥታ የማስፈንና ወደተለያዩ አዳዲስ ጣቢያዎች የማዘዋወር ሥራ እየተሰራ መሆኑን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በዚህም መሰረት በማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ስደተኞች መደበኛ አገልግሎት ተጀምሯል ተብሏል። በነዚህም የመጠለያ ጣቢያዎች 9 ሺህ ያህል ስደተኞች የሰብዓዊ አገልግሎት እርዳታ እንዳገኙም በመግለጫው ሰፍሯል።

በትግራይ ክልል ተበታትነው የሚገኙ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ወደሚገኙ ከተሞች የፈለሱ ስደተኞች ምዝገባም እየተከናወነ እንደሆነም ተገልጿል።

እንደ ኤጀንሲው ከሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ከ5 ሺህ 200 በላይ ስደተኞች የተመዘገቡ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ምዝገባው ቀጥሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ኤጀንሲው ቁጥሩን በትክክል ባያስቀምጥም በርካታ ስደተኞች ወደ አፋር ክልል በራህሌ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለማዘዋወር እንደተቻለም ተቀምጧል።

የስደተኞቹን ደኅንንት ለመጠበቅም የጣቢያዎቹን ፀጥታ የማስፈን ሥራዎችም እየተሰሩ ነው ብሏል መግለጫው።

ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ ሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ ንብረቶች ተዘርፈዋል እንዲሁም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

ለህይወታቸው የሰጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞችም ተፈናቅለዋል።

በዚህ ጦርነትም ከአንድ ወገን ወይም ከሌላ ወገን ጋር ትስስር አላችሁ በሚል የአፀፋ ጥቃቶች፣ አፈናዎች፣ እስሮችና ጠለፋዎች እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ተዓማኒ እና የተረጋገጠ ዘገባ እንደደረሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

የተመድ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በተጨማሪም በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በጣም ከባድ የሆኑ የጥቃት ክሶች ሪፖርቶችን ሰምተናል በማለትም የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት በእነዚህ ተዓማኒ ክሶች ላይ መደበኛ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በማይ አይኒ እና በአዲ ሃሩሽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በተለያዩ ታጣቂ አካላት በምሽት የሚፈፀመው የወንጀል ድርጊቶችም እንደሚረብሹም ተመድ ገልጿል።

ተመድ ጥቃቶቹ በተለያዩ ታጣቂ አካላት ይፈፀማል ቢልም መንግሥት በበኩሉ ህወሓት ስደተኞቹ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች አዳዲስ ጥቃቶችን እየፈፀመ ነው ብሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በማይዓይኒ እና በአዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያች የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወድቋል ብለው በማሰባቸው ጥበቃ ወዳለበት አካባቢዎች እንዲዛወሩ ጠይቀዋል ብሏል።

በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና እንዲሰጣቸው እና ወደ ሦስተኛ አገር እንዲዛወሩ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ተብሏል።

መንግሥትም ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር እየሰራ ነው ተብሏል።

ከኅዳር ወር ጀምሮም በሁለት የኤርትራውያን የስደተኛ መጠለያዎች፣ ሽመልባ እና ህጻጽ ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ህወሓት ፈፅሟል እንዲሁም የስደተኛ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ አድርጓል በማለትም ወንጅሎታል።

በታኅሣሥ ወር የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ኤጀንሲ የበላይ ኃላፊ በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በግዴታ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስለመደረጉ፣ ስለ መታገታቸውንና መገደላቸው መስማታቸው በመግለጽ “እጅጉን ስጋት እንደፈጠረባቸው” ተናግረው ነበር።

ፊሊፖ ግራንዴ እንዳሉት እንዲህ አይነት ድርጊት ከተረጋገጠ፣ ዋነኛ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው ብለዋል።

በባለፉት ሳምንታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች በሽረ መታሰራቸውን ተመድ የገለፀ ሲሆን ኤጀንሲው በቅርቡ ከሽረ ለመውጣት 79 ስደተኞች ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው።

እነዚህ ስደተኞች ወደ በራህሌ እንዲጓዙ ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ጥያቄ ቀርቦ ክትትልም እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።

በሽመልባ እና ህጻጽን ለቀው ለወጡ ስደተኞችም ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ዓለም ዋጭ ተብሎ በሚጠራ ቦታ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ እየተቋቋመም ነው ተብሏል።

ኤጀንሲው በአዲሱ መጠለያ ጣቢያ ለማስፈር እና በድጋፍ ላይ የተመሠረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና ለመስጠት እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል።

ሆኖም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚጠበቀው ድጋፍ አለመገኘቱ በተጠበቀው ደረጃ እየሄደ አይደለም በማለትም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያግዝ ጥሪ ቀርቧል።

“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውጤታማ እና ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረግ ስደተኞችን በአዲስ መጠለያ ጣቢያ የማስፈሩን ሂደት ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል ኤጀንሲው በመግለጫው።

ከዚህም በተጨማሪ ለስደተኞች የሚደረገው ጥበቃ እንደሚቀጥልና የበቀል ጥቃቶች፣ አፈናዎች፣ እስሮች እና ሁከቶች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎችን እንዲደግፍና እንዲያወግዝም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ቀርቧል።

ተመድ በበኩሉ በትናንትናው መግለጫው የስደተኞቹ ደኅንነት እንዲጠበቅ የጠየቀ ሲሆን የወደሙት የሽመልባና ህጻጽ ይኖሩ ለነበሩ ስደተኞች አዲስ መጠለያ ይገንባ ብሏል።

ስደተኞቹንና ሌሎች ሁለት ሚሊዮን ተፈናቃዮችን መርዳት ይቻል ዘንድ ገንዘብና ነዳጅ ማግኘት እንዲቻል እንዲሁም መሰረታዊ የሚባሉ የኤሌክትሪክ፣ መብራትና የባንክ አገልግሎቶችም እንዲመለሱ ጠይቋል።

በሽረና መቀለ የሚገኙ አየር ማረፊያዎች ጅማሮ፣ ወደ ትግራይ የሚያገናኙ መንገዶችን መክፈትም ለስደተኞቹም ይሁን በትግራይ ክልል ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች መሰረታዊ ነው ብለዋል።