1 ነሐሴ 2021, 09:56 EAT

የኮሮና ህመምተኛ

በኢትዮጵያ ሶስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየጀመረ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ እንደ ማሳያነት የጠቀሳቸውም በኮሮናቫይረስ ይያዙ የነበሩ ሰዎች ከሶስት ሳምንት በፊት ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ጭማሬ አሳይቷል ብሏል።

ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት በአማካኝ በአንድ ቀን 70 ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው ይመዘገብ የነበረ ቢሆንም ሐምሌ 22 ቀን 476 ግለሰቦች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገልጿል።

ይህ ቁጥርም ሁለተኛው ዙር ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ሆኖም መመዝገቡንም ተቋሙ አሳውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ናሙና ከሚሰጡ 100 ግለሰቦች 1 እስከ 2 ግለሰቦች የመያዝ ምጣኔ የነበረ ሲሆን ሐምሌ 22 ቀን ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሮ ወደ 7 ግለሰቦች የመያዝ ምጣኔ ከፍ ብሏል።

በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚገኙ ህሙማን ከሶስት ሳምንት በፊት በአማካኝ 124 ግለሰቦች የነበሩ ሲሆን ሐምሌ 22 በእጥፍ በመጨመር ወደ 228 ማደጉም ተገልጿል።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት መረጃዎች እና ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ታውቋል።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የኮቪድ-19 ዴልታ ቫይረስ ሲሆን በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የዴልታ ቫይረስ መኖሩ ባይረጋገጥም የሶስተኛ ዙር ወረርሽኝ መከሰቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር ካበቃ በኋላ በተወሰነ መልኩ በማህበረሰቡ መዘናጋቶች እንዲሁም የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች በአግባቡ ባለመተግበራቸው ሶስተኛው ዙር ሊከሰት የሚችልበት ምልክቶች እየታዩ ነው።

ተቋሙ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎቹ እንዲከበሩና ማስክ ማድረግ፣የእጅን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እና ርቀትን በመጠበቅ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የኮቪድ-19 መከላከከልና መቆጣጠር እንደሚቻልም አሳሳስቧል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 279 ሺህ 629 ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 263 ሺህ 392 ግለሰቦች ከኮቪድ-19 ቫይረስ አገግመዋል እንዲሁም 4 ሺህ 381 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አገሪቷ በአጠቃላይ 3,006,482 ምርመራዎችን አካሂዳለች።