1 ነሐሴ 2021, 07:59 EAT

አቤል ታስማን የተባለው የደች አሳሽ እአአ በ1642 ወደ ደቡብ የምድራችን ክፍል ጉዞ ሲያደርግ አንድ አህጉር እንዳለ እርግጠኛ ሆኖ ነበር።
ለየት ባለ ጢሙ የሚታወቀው አቤል ፍትሕን ለማስፈን በሚል በሚወስደው ቆፍጣና እርምጃ ስሙ ይነሳል።
በዚያ ዘመን ደቡባዊው የምድራችን ክፍል ለአውሮፓውያን እንግዳ ነበር። በዚህ አካባቢ ‘ቴራ አውስትራሊስ’ የተሰኘ ሰፊ መሬት እንዳለ ይገምቱ ነበር።
ከጥንታዊ የሮማውያን ዘመን አንስቶ ስለዚህ የዓለም ክፍል መላ ምቶች ነበሩ። ስለ አካባቢው የማወቅ ጉጉት ዘመናት ተሻግሯል።
አቤል ከኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ሁለት አነስተኛ መርከቦች ይዞ ወደ ምዕራብ ከዚያም ወደ ሰሜን አስከትሎም ወደ ምሥራቅ ጉዞ የጀመረው ነሐሴ 14 ነው። በስተመጨረሻ የኒው ዚላንድ ደቡባዊ ደሴት ደረሰ።
ለዘመናት በዚያ መሬት የኖሩት የሞሪ ሕዝቦች የአቤል መምጣት አላስደሰታቸውም።
ደሴቱ ጋር በደረሰ በሁለተኛው ቀን ነዋሪዎቹ በጀልባ ወጡ፤ በደች መርከቦች መካከል መልዕክት የሚያመላልስ አነስተኛ መርከብ ላይም ጥቃት ተሰነዘረ። አራት አውሮፓውያንም ተገደሉ።
- የዓሳ ጥሬ ሥጋ እንደ በሬ ቁርጥ የሚቸበቸብባት ሐዋሳ
- ባሕር ዳርን ‘የኪነ ጥበብ መዲና’ ለማድረግ የሚተጋው ወጣት
- አንዲት ቤተክርስቲያንን ጠብቀው ያቆዩት ኢትዮጵያዊ ሼኽ
አውሮፓውያኑ በምላሹ 11 ጀልባዎች ላይ መድፍ ተኮሱ። ጀልባዎቹ ምን እንደሆኑ ግን አይታወቅም።
አቤል አካባቢው ‘ሙራንደርስ’ ብሎ ከጠራው በኋላ የደሴቱን መሬት እንኳን ሳይረግጥ ከሳምንታት በኋላ ተመለሰ።
በዘመኑ ብዙ ይባልለት የነበረውን ደቡባዊ አህጉር እንዳገኘ አምኖ ነበር። እንዳሰበው ንግድ የጦፈበት ቦታ አልነበረም። እሱም ዳግመኛ ወደ እዚያ ስፍራ አልተመለሰም።
በዚህ ወቅት አውስትራሊያ አውሮፓውያን ያስሱት የነበረው አህጉር እንደሆነ አያውቁም ነበር።

የዚላንዲያ መገኘት
2017 ላይ ጂኦሎጂስቶች ዚላንዲያ የተባለ 1.89 ሚሊዮን ስኩዌር ማይል ስፋት ያለው አህጉር እንዳገኙ አስታወቁ። አህጉሩ ከማዳጋስካር ስድስት እጥፍ ይበልጣል።
አህጉሩ በሞሪ ቋንቋ ቴ ሩ-አ-ማይ ይባላል።
በምድራችን ሰባት አህጉሮች እንዳሉ ሲነገር ቢቆይም ጂኦሎጂስቶቹ ግን ስምንተኛ አህጉር አለ ብለዋል።
ስምንተኛው አህጉር የምድራችን ትንሹ፣ ስሱና አዲሱ በመሆን የሚበልጠው አህጉር የለም።
ይህ አህጉር 94 በመቶ መሬቱ ከውሃ በታች ነው። ጥቂት የአህጉሩ ክፍል ብቻ ነው ደሴት። ይህም ኒው ዚላንድን ይጨምራል።
በኒው ዚላንድ ክራውን የጥናት ተቋም የሚሠሩት ጂኦሎጂስት አንዲ ቱሎች ዚላንድያን ያገኘው ቡድን አባል ናቸው። አህጉሩ በግልጽ የሚታይ ቦታ ቢሆንም በጥናት ለማግኘት ግን ዓመታት መውሰዱን ይናገራሉ።
ይህ አህጉር አሁንም ምስጢራዊና አስደናቂ ነው። ብዙ የማይታወቁ እውነታዎችን ከሁለት ኪሎ ሜትር ውሃ በታች ይዟል። አህጉሩ እንዴት ተፈጠረ? እዚያ ምን ይኖር ነበር? በውሃ ከተሸፈነ ምን ያህል ዓመታት አስቆጠረ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ዚላንዲያ– ስምንተኛው አህጉር
ስለ ዚላንዲያ ማጥናት ቀላል አይደለም።
አሳሹ አቤል በ1642 ኒው ዚላንድን ካገኘ በኋላ፤ እንግሊዛዊው ካርታ ነዳፊ ጄምስ ኩክ ወደ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ለሳይንሳዊ ጥናት ተልኮ ነበር።
ቬነስ በምድር እና በፀሐይ መካከል ስታልፍ እንዲመለከትና ፀሐይ ምን ያህል እንደምትርቅ እንዲያሰላ ነበር የተላከው።
ይህን ተልዕኮ ሲያጠናቅቅ የሚያነበው መልዕክት በፖስታ ተሰጥቶትም ነበር። መልዕክቱ ከፍተኛ ምስጢር ሲሆን አሳሹ ደቡባዊውን አህጉር እንዲያገኝ ያዛል።
እንዲያገኝ የተላከውን አህጉር በመርከብ አልፎ ኒው ዚላንድ እንደደረሰ ታሪክ ያትታል።
ዚላንዲያ አህጉር እንዳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጨባጭ ጥቆማ የተገኘው በስኮትላንዳዊው ሰር ጄምስ ሄክተር አማካይነት ነው። እአአ በ1895 በኒው ዚላንድ ዳርቻ የሚገኙ ደሴቶችን ለመመርመር ተጉዟል።
ከምርምሩ በኋላ ኒው ዚላንዲያ የቅጥልጥል ተራራ አህጉር ቅሪት እንደሆነች ደመደመ። ይህ ተራራማ አህጉር ከደቡብ ወደ ምሥራቅ የተዘረጋ ሲሆን፤ በጊዜ ሂደት በውሃ ተውጧል።
2017 ላይ የተደረገውን ጥናት የመራው ጂኦሎጂስት ኒክ ሞርታይመር እንደሚለው፤ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ስለ ዚላንዲያ ብዙም ምርምር ሳይደግ ቆይቷል።
አህጉር ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። በጣም ውድም ነው። ጂኦሎጂስቶች አህጉር ብለው ስም የሚሰጡት ከፍታማ ለሆነ፣ የተለያዩ አለቶች ላሉት፣ ግዙፍ አካባቢ ነው።
ስለዚህም ዚላንዲያን አህጉር ለማለት አስፈላጊ ማስረጃዎችን መሰብሰብ ነበረባቸው።
በ1995 አሜሪካዊው ጂኦፊዚሲስት ብሩስ ሉየንደርክ ዚላንዲያን አህጉር ብሎ ከጠራ በኋላ ጥናቱ ተጧጧፈ።
የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ስምምነት እንደሚለው፤ አገራት ከግዛታቸው ውጪ በ370 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ያለ የተፈጥሮ ሀብት ላይ የባለቤትነት ጥያቄ የማንሳት መብት አላቸው።
ይህ ማለት ኒው ዚላንድ የአዲሱ አህጉር አካል እንደነበች ካስመሰከረች ግዛቷን በስድስት እጥፍ ታሳድጋለች ማለት ነው።

አለት እና ሌሎችም ማስረጃዎች ሲሰባሰቡ ዚላንዲያ አህጉር መሆኗ ወደ መረጋገጥ ተቃረበ። የመጨረሻው ማስረጃ የሳተላይት ምስል ነው። ምስሉ መሬት ላይ በተለያየ ወቅት የነበረውን ለውጥ በመመዝገብ ማስረጃ ያቀርባል።
ዚላንዲያ ለዓለም ሕዝብ ሲተዋወቅ በምድር ላይ ካሉ የውሃ አካላት ይዞታዎች ትልቁ እንደሆነ ታውቋል።
ጂኦሎጂስት ኒክ ሞርታይመር “ደስ የሚል አካባቢ ነው። እያንዳንሁ አህጉር በውስጡ የተለያዩ አገሮች አሉት። ዚላንዲያ ግን ባለ ሦስት ግዛት ነው” ይላል።
አህጉሩ ከኒው ዚላንድ በተጨማሪ ኒው ካሊዶኒያ የተባለ ደሴት እና ሎርድ ሆዌ የተባለ የአውስትራሊያ ክፍል የሆነ ደሴት በውስጡ ይዟል።
ባለ ብዙ ምስጢሩ አህጉር
ዚላንዲያ ከ550 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የነበረው የጥንታዊው ጎንድዋና አህጉር አካል ነው። ምዕራብ አንታርክቲካ፣ ምሥራቅ አውስትራሊያና ሌሎችም አጎራባቾች አሉት።
ይህ አካባቢ የደቡብ ንፍቀ ክበብ አካል ሆኖ ቆይቶ ከ105 ሚሊዮን ዓመታት በፊት እስካሁን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተነጥሎ መውጣት ጀመረ።
አህጉሩ በጊዜ ሂደት ነው ውሃ የለበሰው። በጣም ስስ አካባቢ ቢሆንም በውስጡ የተገኙት አለቶች አህጉር እንደሆነ ይጠቁማሉ።
አለቶቹ ከኢግኒየስ፣ ከሜታሞርፊክ እና ከሴድመንተሪ የተሠሩ ሲሆኑ፤ የአህጉሩ ውቅያኖስ ወለል ከባዛልት የተፈጠረ ነው።
አሁንም ድረስ ስለ ስምንተኛው አህጉር ብዙ የማይታወቁ እውነታዎች አሉ።
ዚላንዲያ በጣም ስስ ሆኖ ሳለ እስካሁን ድረስ ተበትኖ ወደ ትንንሽ አህጉሮች ሳይከፋፈል ለምን እንደቆየ አልታወቀም።
ለምን ውሃ እንደለበሰ፣ ውሃ ከመልበሱ በፊት ደረቅ መሬት ይሁን አይሁን ገና አልተደረሰበትም።
ከጥቂት የአህጉሩ ደሴቶች በተጨማሪ አብዛኛው መሬት ከድሮውም ውሃ የለበሰ መሬት ነበረ ብለው የሚከራከሩ ተመራማሪዎች ያሉ ሲሆን፤ ቀድሞ ደረቅ መሬት እንደነበረ የሚያምኑ ባለሙያዎችም አልታጡም።
ባለ 101 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ የአየር ንብረቱ ወይና ደጋማ ነው። በቀድሞው ጎንድዋና ግዛት የተለያዩ እጽዋት እና እንስሳት ይኖሩ ነበር።
እንስሳቱ ከትንንሽ ፍጥረቶች እስከ ግዙፉ ታታኖሰረስ ይደርሳሉ።
ዳይኖሰሮች
በደቡብ ንፍቀ ክበብ የግዙፍ እንስሳትን ቅሪተ አካል ማግኘት የተለመደ ባይሆንም እንደ ዳይኖሰር ያሉ የእንስሳት ቅሪት አካል ተገኝቷል።
በ1960ዎቹ ኒው ዚላንድ ውስጥ የዳይኖሰር የጎን አጥንት መገኘቱ ይታወቃል።
2006 ላይ በቀላሉ የማይገኝ ሥጋ በል እንስሳ የእግር አጥንት ተገኝቶ ነበር። እንስሳው አሉሶር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። የተገኘውም በቻታም ደሴት ላይ ነው።
እነዚህ ቅሪተ አካሎች እንደሚያሳዩት እንስሳቱ የነበሩት ዚላንዲያ ከጎንድዋና ከተገነጠለ ወዲህ ነው።
በእርግጥ ይህ ማለት ዳይኖሰሮች በመላው ዚላንዲያ ውስጥ ኖረዋል ማለት ላይሆን ይችላል።
በቪክቶሪያ ዩኒቨርስ የጂኦፊዚክስ ፕሮፌሰሩ ሩፐርት ሱተርላንድ፤ አህጉር ሳይኖር ግዙፍ እንስሳት ይኖራሉ? ወይስ አህጉር ሲጠፋ እንስሳቱም ይጠፋሉ? የሚለው አከራካሪ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለምሳሌ ኒው ዚላንድ ውስጥ ኪዊ የሚባል የወፍ ዝርያ አለ። ከአንድ የአዕዋፍት ቤተሰብ የሚገኘው ሌላ ወፍ ደግሞ ሞዋ ይባላል። ከ500 ዓመታት በፊት ከምድረ ገጽ እስኪጠፉ ድረስ በአንድ አህጉር ኖረዋል።
ኤለፋንት በርድ የሚባለውና ከእነዚህ አዕዋፍት የሚገዝፈው ወፍ ከ800 ዓመታት በፊት በማዳጋስካር ደን ውስጥ ይኖር ነበር።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት እነዚህ አዕዋፍት በጎንድዋና ውስጥ ከሚኖር የወፍ ዝርያ የተገኙ ናቸው።
አህጉሩ በ130 ሚሊዮን ዓመታት ሲበታተን ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ ማዳጋስካር፣ አንታክቲካ፣ አውስትራሊያ፣ የአረብ ሰርጥ፣ የሕንድ አህጉር እና ዚላንዲያ ተፈጠሩ።
ይሄ ማለት ደግሞ ዚላንዲያ ከባሕር በላይ ነበር ማለት ነው። ከ25 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ግን መላው አህጉሩ በውሃ ሰጠመ። ምናልባትም ኒው ዚላንድም የዚህ አካል እንደነበረች ይታመናል።
ፕሮፌሰር ሩፐርት እንደሚሉት፤ እንስሳት እና እጽዋት ከዚህ ለውጥ በኋላ ተስፋፍተው ሊሆን ይችላል።
ከዚላንዲያ ቅሪተ አካል ለመሰብሰብ ባይቻልም ከባሕር በታች ያሉ ጥቃቅን ቅሪቶችን ማጥናት ይቻላል።
2017 ላይ አንድ አጥኚ ቡድን 1,250 ሜትር ቆፍሮ የተለያዩ ዝርያዎች አግኝቷል። የእጽዋት ቅሪት እንዲሁም የነፍሳት ቅሪትም አግኝተዋል።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ እጽዋት መገኘታቸው ዚላንዲያ በአንድ ወቅት ሙሉ በሙሉ ውሃ ያልለበሰ መሬት እንደሆነ ይጠቁማል።

ልዩ ቅርጽ
ከኒው ዚላንድ ቅርጽ ሁለት አስገራሚ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ። አንደኛው በደቡባዊ ደሴት በኩል ያለው ዝርግ መሬት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በተቀረው አካባቢ የሚገኘው የታጠፈ መሬት።
ሁለቱ ቅርጾች በአግድሞሽ መስመር ይለያያሉ። ይህ መስመር ፓሲፊክ እና አውስትራሊያን ቴክቶኒክ ፕሌቶች (የመሬት የላይኛው ሽፋን) የሚገናኙበት ነው።
ለዚህ ለየት ያለ ቅርጽ መፈጠር እንደ ምክንያት የሚቀመጠው ቴክቶኒክ ፕሌቶች መንቀሳቀሳቸው እንደሚሆን መላ ምቶች ቢኖሩም እርግጠኛ መረጃ ገና አልተገኘም።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ይህንን አህጉር የሚመለከቱ መረጃዎች ባጠቃላይ እስኪታወቁ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።
“ሁሉም ነገር ከሁለት ኪሎ ሜትር በታች በውሃ ሲሸፈን ምርምርን ከባድ ያደርገዋል” ይላሉ።
አቤል ይህንን አህጉር ለማግኘት ከተነሳበት ዘመን 400 ዓመታት በኋላ ስምንተኛው አህጉር መኖሩ ተደርሶበታል።
በእርግጥ በቂ መረጃ ለማግኘት ሰፊ ጊዜ፣ ገንዘብ ያሻል።