የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ካርቱም ያጓጓዝኳቸው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ናቸው ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጠ።

አየር መንገዱ እንዳለው መሳሪያዎቹ ወታደራዊ ሳይሆኑ ለአደን አገልግሎት የሚውሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ አስፈላጊው ሕጋዊ የመጓዣ ሰነድ ያላቸው ናቸው ብሏል።

አየር መንገዱ የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ሱና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘው ሱዳን የገቡት ጦር መሳሪያዎች “[በሱዳን] መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም” ጥቅም ላይ ሊውሉ ነበር የሚል ጥርጣሬ አለ ሲል ያወጣውን አጣጥሏል።

ሱዳን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ካርቱም ከገቡ በኋላ ተይዘዋል ስላለቻቸው የጦር መሳሪዎች ምርመራ እያደረኩ ነው ስትል ማስታወቋ ይታወሳል።

እንደ ሱና ዘገባ ከሆነ መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ቅዳሜ ምሽት ካርቱም ባረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ተጭኖ የነበረ ጦር መሳሪያ በሱዳን ጉምሩክ ባለሥልጣናት ተይዟል።

አየር መንገዱ ምን አለ?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሱና ላይ የወጣውን ዘገባ የተሳሳት ነው ያለ ሲሆን፤ ወደ ካርቱም ያጓጓዛቸው የአደን ጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ሰነድ እንዳላቸው ገልጿል።

አየር መንገዱ “ወደ ሱዳን የተጓጓዙት ጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ እንዲሁም ከተቀባይና ከላኪ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ያሉት የንግድ ለአደን የሚውሉ ጦር መሳሪያ ትራንስፖርት ነው” ብሏል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ።

ሱና የጦር መሳሪያዎቹን ጉዳይ እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ጦር መሳሪያዎቹ ከሩሲያ ሞስኮ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ለሁለት ዓመታት ተቀምጠው ለሱዳን መንግሥት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ በሲቪል አውሮፕላን ወደ ካርቱም እንዲጫኑ አዲስ አበባ ፈቅዳለች ማለቱን አስነብቦ ነበር።

ኮሚቴው ጨምሮም ጦር መሳሪያዎች በ72 ሣጥኖች መጓጓዛቸውን እና በውስጡም ከጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ በጨለማ መመልከት የሚያስችሉ መነጽሮች ይገኙበታል ብሏል።

አየር መንገዱ በበኩሉ የጦር መሳሪያዎቹ አዲስ አበባ በሚገኙ የደኅንነት ባለስልጣናት ለረዥም ጊዜ የማጣራት ሥራ ሲከናወንባቸው ቆይቷል ይላል።

በዚህም የተነሳ የጦር መሳሪያው ተቀባይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያዎችን እንዲልክ አልያም ወደ 250 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ካሳ እንዲከፈለው በሱዳን ፍርድ ቤት አየር መንገዱን መክሰሱን ገልጿል።

አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ደኅንነት ኃላፊዎች የማጣራት ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ጦር መሳሪያውን ለማጓጓዝ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በሱዳን ለሚገኘው ተቀባይ ጦር መሳሪያውን አጓጉዘናል ብሏል።

አየር መንገዱ ከዚህ በተጨማሪም የመሳሪያው መጓጓዝ ሕጋዊነትን የሚያረጋግጥ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተጻፈ ደብዳቤ አለኝ ብሏል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት መሻከር

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ይገባኛል በሚሉት የድንበር ቦታ እና በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በመካከላቸው ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።

ኢትዮጵያ የትግራዩ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በአልፈሽጋ የነበራትን ጦር ካንቀሳቀሰች በኋላ ሱዳን የድንበር ቦታውን ተቆጣጥራ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሱዳን የያዘችውን መሬት ለቅቃ እንድትወጣ ሲጠይቅ ቢቆይም የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን መሬቱ የሱዳን እንደሆነ በመግለጽ ለቀው እንደማይወጡ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊትም የሱዳን መሪዎች በአልፋሽጋ አካባቢ የገነቧቸውን መሠረተ ልማቶች አስመርቀው ነበር።

በሌላ በኩል ከሦስት ቀናት በፊት ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከሱዳን ሰርጎ ለመግባት የሞከረ የህወሓት ቅጥረኛ ኃይልን ደመሰስኩ ማለቷ ይታወሳል።

የአገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ኮሎኔል ሰይፈ ኢንጊ፣ በሰዱን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ የተባለው ኃይል የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ጥቃት ለመሰንዘር እንደነበር አመልክተዋል።

ጨምረውም ቡድኑ የተለያዩ ፀረ ሰው እና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ ሞክሮ ነበር ስለማለታቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት አስታውቆ ነበር።

ቢቢሲ