29 መስከረም 2021, 07:04 EAT

ሆዷን የያዘች ሴት

ጽጌሬዳ ትውልድ እና እድገቷ በአዲስ አበባ ነው። የወር አበባ ማየት ከጀመረችበት እድሜዋ ጀምሮ በየወሩ በከፍተኛ ሕመም ውስጥ እንደምታልፍ ትናገራለች።

ጽጌረዳ ተማሪ በነበረበችበት ወቅት የወር አበባዋ በሚመጣበት የመጀመሪያ ቀን በትምህርት ገበታዋ ላይ አትገኝም ነበር። የሕመም ስሜት መሰማት የሚጀምረው 10 ቀናትን ቀደም ብሎ ቢሆንም በመጀመሪያው ዕለት ግን የማያላውስ ሕመም ከቤት ያውላታል።

“የወር አበባዬ ከመምጣቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሕመሞቹ ይበረታሉ። ወይ እግሬ ያብጣል፤ ወይ ከፍተኛ ሙቀት ይሰማኛል። በየወሩ የሚሰማኝ ሕመም ይለያያል። ተማሪ እያለሁ እንደ ነገ እንደሚመጣ ሳውቅ ከትምህርት ቤት እቀር ነበር። ትምህርት ቤት ከሄድኩኝ እንኳን ትቼ ወደ ቤቴ እመለስ ነበር” ስትል ታስታውሳለች።

የሥራውን ዓለም ከተቀላቀለች ወዲህም የወር አበባዋ ከመጣ ሥራ አትገባም። አስገዳጅ ሥራ ከገጠማት እንኳን የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቷን እጥፍ አድርጋ ካልዋጠች መቆምም መራመድም የሚከለክል ሕመም ይሰማታል።

በርካታ ወንዶች የወር አበባ ሕመም ምን ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሕመሙንም ለመረዳት ይጠይቃሉ። ከሆድ ቁርጠት፣ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ የድባቴ እና ጭንቀት ስሜቶች እንዲሁም ድካም በርካታ ሴቶች በወር አበባ ወቅት ያጋጥማቸዋል።

በኔዘርላንዱ ራድባውንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው የሕክምና ማዕከል ከ43 ሺህ በላይ ሴቶች የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው፤ 85 በመቶው በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ ሕመም ያለው ቁርጠት ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም 77 በመቶው የስሜት መረበሽ ውስጥ ሲገቡ 71 በመቶው ዝለት እና ድካም ያጋጥማቸዋል።

ከአጠቃላይ የዓለማችን ሕዝብ 3.9 ቢሊዮኑ ሴቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም የሴቶች ቁጥር ከወንዶች የሚበልጥ መሆኑን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ ያሳያል።

በሠራተኛው ኃይል ውስጥም የሴቶች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። የዓለም ባንክ ከሦስት ዓመታት በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በመላው ኢትዮጵያ ካለው ሠራተኛ ኃይል ውስጥ 46.5 በመቶውን የያዙት ሴቶች ናቸው።

የሴታዊት ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ህይወት አበበ እንደምትለው ታዲያ የኢትዮጵያ የአሰሪ እና ሠራተኛ ሕግ እነዚህን ሴት ሠራተኞች ከማገናዘብ አንጻር ተራማጅ የሚባል ነው። በተለይም የእናትነት እረፍትን በማካተት ረገድ ሕጉ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ለሴቶች ትኩረት የሰጠ ነው ትላለች።

ነገር ግን በዚህ ሕግ ውስጥ ሴቶች በየወሩ የሚያጋጥማቸውን ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ሕመም ከግምት ውስጥ የሚከት እረፍት እንዲሰጥ ለማድረግ ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ዘመቻዎችን ማካሄድ መጀመራቸውንም ታክላለች።

ሴታዊት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚባል ደረጃ ሴት ሠራተኞችን የያዘ ተቋም ሲሆን በጉዳዩ ላይ ቅስቀሳ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ሠራተኞች ይህንን የወር አበባ እረፍት መስጠት መጀመሩንም ህይወት ለቢቢሲ ትናገራለች።

ሆዷን እና ራሷን የያዘች ሴት

ይህንን ፈቃድ በመስጠታቸውም እስካሁም በሥራ ውጤታማነት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ለውጥ እንዳላዩ ትገልጻለች።

“የወር አበባ ሕመም ከሰው ሰው ይለያያል። እኛ ቢሯችን ውስጥ ከሁለት እስከ አምስት ቀን በሚል ነው የተገበርነው። ነገር ግን አንድ ሴት አንድ ቀን ከፈለገች ልትወስድ ትችላለች። እንዲሁም በሥራ ገበታዋ መገኘት ከቻለች ትገኛለች። ከቤቷ ሆና መስራት ከመረጠችም በእነዚህ ቀናት ከቤት መስራትም እንድትችል እንፈቅዳለን” ስትል ህይወት ታብራራለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የወር አበባ እረፍትን የሚቃወሙ አካላት አንዳንድ ሴቶች ሕመም ባይኖራቸውም እንኳን እረፍቱን ያለ አግባብ ሊጠቀሙት ይችላሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

አክለውም ሴቶችን መቅጠር ለአሰሪዎች አክሳሪ እንደሆነ እንዲሰማቸው ያደርጋል ይላሉ።

ሴቶች የወሊድ ፈቃድን ጨምሮ ባለባቸው የቤተሰብ ኃላፊነት ምክንያት በሠራተኛው ኃይል ውስጥ ያላቸውን ተፈላጊነት የሚቀንስ ተጨማሪ ሰበብ ይሆናል ሲሉም ይከራከራሉ።

ህይወት ለዚህ ስትመልስ “ይህ የጾታ ብቻ ሳይሆን የሰብአዊነት ጉዳይ ነው፤ እነዚህ ክርክሮች ኢ-ሰብአዊ ናቸው” ትላለች።

“ዓለማችን ለሁሉም ሰው ምቹ የሆነች እና ሁሉም ሰው እኩል እድል የሚያገኝባት እንድትሆን ከፈለግን እንደ የወር አበባ ያሉ ሰውነታችን ለሚያልፍባቸው ሂደቶች ፈቃድ መስጠት ይገባናል” ሰትል ታስረዳለች።

“ሴቶች በከፍኛ ስቃይ ውስጥ እያለፉ ሥራ ይግቡ ማለትም ጭካኔ ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

በወር አበባ ወቅት ከሚያጋጥሙ ሕመሞች ባሻገርም በመጀመሪያ ቀናት ያለው የፍሰት መጠን ሴቶችን ጭንቀት ውስጥ ይከታቸዋል።

ጽጌሬዳ ግንቦት አካባቢ ያለው የከረረ ፀሐይ በመጣ ቁጥር ሁል ጊዜም ምቾት የማይሰጣት የትምህርት ቤት ትዝታዋ እንደሚመጣ ትናገራለች።

“ግንቦት ላይ ከፍተኛ ሙቀት አለ። የንጽህና መጠበቂያዬን ለመቀየር የእረፍት ጊዜ እስከሚመጣ እጠብቃለሁ። በሙቀቱ ብዛትም የወር አበባዬ ልብሴን እንዳይነካ ስለምጨነቅ ከውስጥ ቁምጣ እደርባለሁ። ይህ ሌላ ሙቀት ይጨምርብኝ ነበር” ትላለች።

ለሴታዊቷ ህይወት ይህን የወር አበባ ፈቃድ ጉዳይን ወደ ትምህርት ቤቶች ለመውሰድ አስበው ከሆነ ጠይቀናታል።

በወር አበባ ላይ እየሰሩ ያሉ ተቋማት በርካታ መሆናቸውን በመግለጽ በትምህርት ቤቶች የንጽህና መጠበቂያዎች በቀላሉ እንዲገኙ እና የተማሪዎች ንቃተ ሕሊና እንዲጨምር የተለያዩ ሥራዎች በቅንጅት እየተሰሩ መሆኑን ትናገራለች።

በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ሴት ተማሪዎች ሕመም በሚበረታባቸው ወቅት ይህንን የወር አበባ ፈቃድ እንዲያገኙ የተጀመረ ጥረት የለም።

ሆዷን የያዘች ሴት

የወር አበባን እንደ ነውር

የወር አበባን እንደ አሳፋሪ እና ነውር መመልከት በኢትዮጵያ፣ በተለይም በከተሞች ከጊዜ ወደ ግዜ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ቀላል የማይባሉ ፈተናዎችን ሴቶች በዚህ ተፈጥሯዊ ሂደት ምክንያት ያልፋሉ።

ጽጌሬዳ የወር አበባ ሲባል ፈርቶ የሚሮጥ የአክስቷን ልጅ እንደ ምሳሌ ታነሳለች።

“የወር አበባ በጣም ይፈራ ነበር። ደም ያስፈራኛል ይል ነበር። ከብዙ ውይይት በኋላ አሁን ሞዴስም የወር አበባም ሲባል ከወንበሩ መነሳት አቁሟል” ስትል በፈገግታ ታስታውሳለች።

ነገር ግን ከወር አበባ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሕመሞችን በተመለከተ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶች በወንዶች ብቻ ሳይሆን በወር አበባ ወቅት ሕመም በማይጠናባቸው ሴቶችም ዘንድ እንዳሉ ትናገራለች።

“ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሥራ ቦታ ‘አጋነሽዋል’ ወይም ‘የውሸትሽን’ ነው የሚሉ አስተያየቶች ያጋጥመኛል” የምትለው ጽጌሬዳ አሟት በተኛችበት ‘ከቦይፍሬንድሽ ጋር ተጣልተሽ ከሆነ ተናገሪ። የወር አበባ እንደዚህ ሊያም አይችልም’ የሚሉ አስተያየቶች ጭምር ታስተናግዳለች።

ጽጌሬዳ እንደ አድል ሆኖ የወር አበባ ዙሪያ የሚሰራው ኖብል ካፕ ውስጥ ነበር የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችው።

በዚህም ምክንያት የወር አበባዋ በሚመጣበት ወቅት ወደ ሥራ ቦታ እንደማትመጣ እና ቀጣሪዋ ድርጅትም እንደሚረዳት ትናገራለች።

ነገር ግን ይህንን ተፈጥሯዊ ሂደት ሁሉም አሰሪዎች እኩል አይረዱትም። በኢትዮጵያ የአሰሪ እና ሠራተኛ ሕግ መሰረትም አንዲት ሴት የወር አበባዋን ተከትለው በሚመጡ ሕመሞች ምክንያት የሐኪም ማስረጃ ካልያዘች በስተቀር፣ እረፍት አታገኝም። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊውን ሂደት እንደ በሽታ የመመመልከት ሥርዓት ይፈጥራል የሚሉ ስጋት አዘል ክርክሮችን ያስነሳል።

ለመሆኑ የወር አበባ ፈቃድ የሚሰጡ አገራት አሉ?

ነገር ግን በዓለም ላይ በተለያዩ አገራት የተለያየ አይነት የወር አበባ ፈቃዶችን በሕግ ደረጃ ያስተዋወቁ አገራት ቁጥር ከፍ እያለ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ አፍሪካዊቷ ዛምቢያ ትገኝበታለች። በዛምቢያ ሴቶች በወር ውስጥ አንድ ቀን ረፍት ይሰጣቸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈር ቀዳጅ የምትባለው ጃፓን ስትሆን የወር አበባ ፈቃድ መስጠት ከጀመረች 71 ዓመታት ተቆጥረዋል። ደቡብ ኮሪያም ይህንን መተግበር ከጀመረች ከ60 ዓመታት በላይ ሆነ።

ደቡብ ኮሪያ ሴት ሠራተኞች በወር ሁለት ቀን የወር አበባ ፈቃድ ከማግኘት አልፎም ይህንን ፈቃዳቸውን ካልተጠቀሙበት በገንዘብ ተሰልቶ እንዲከፈላቸው ታደርጋለች። ታይዋን ሦስት ወር አበባ ፈቃድ ቀናትን ትሰጣለች።

የወር አበባ ፈቃድ በቻይና እና በሕንድም ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል። የተወሰኑ የቻይና ግዛቶች ፈቃዱን አጽድቀዋል። አስገዳጅ ሕግ በሌለባቸው አገራት ድርጅቶች በውስጥ ፖሊሲያቸው ሴቶች በየወሩ የሚያጋጥማቸውን ይህንን ሕመም ያማከለ ፈቃድ ማስተዋወቅ ጀምረዋል።

በኢትዮጵያም ይህንን ሃሳብ ለማስተዋወቅ ሦስት ሴቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማት ዘመቻዎችን ማካሄድ ጀምረዋል። ሴታዊት፣ ኖብል ካፕ እና አዲስ ፓወር ሐውስ ጉዳዩ አጀንዳ እንዲሆን እና በአሰሪ እና ሠራተኛ ሕጉ ውስጥም እንዲካተት ለማስቻል አቅደው እየሰሩ ነው።

“ይህ ጉዳይ የተሸፋፈነ እና ድብቅ ጉዳይ ስለሆነ በቅድሚያ ሰዎች በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንዲጀምሩ ማድረግ እንፈልጋለን” ስትል የሴታዊቷ ህይወት ትናገራለች።

ጽጌሬዳ ወደ ፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የወር አበባ ከፍተኛ ሕመም እንዳለው ቀጣሪዎች ተረድተው ሴቶች በዚህ ጊዜ የሥራ ጫና የሚቀነስበት፤ ሥራ እየሰሩም ቢሆን ሕመማቸው ከግምት የሚገባበትን ጊዜን ለማየት ትናፍቃለች።https://bbc.com/ws/av-embeds/cps/amharic/news-58655685/p07bhh2q/amየተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

በማላዊ የንፅህና መጠበቂያ ፓድ ዋጋ ውድ ነው። በዚህም የተነሳ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ይቀራሉ።