ከ 7 ሰአት በፊት

ኮሮናቫይረስን ለማከም በሙከራ ላይ ያለው መድኃኒት ሞትን ብሎም በጽኑ ታሞ ወደ ሆስፒታል የመግባት መጠንን በግማሽ ሊቀንስ እንደሚችል ጊዜያዊ የክሊኒካል ሙከራ ውጤት አመለከተ።
ሞልነፒራቪር የተሰኘው ይህ የሚዋጥ እንክብል በኮሮናቫይረስ ለተያዙ ሰዎችን በቀን ሁለት ጊዜ እንዲወስዱ በማድረግ ነበር የተሞከረው።
የአሜሪካው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ የሆነው መርክ እንዳለው በሙከራው የተገኘው ውጤት እጅግ አበረታች ነው።
መድኃኒቱን በአሜሪካ ውስጥ ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል በመጪዎቹ ሁለት ሳምንት ውስጥ ለፈቃድ ሰጪው ተቋም ማመልከቻውን እንደሚያስገባም መርክ ገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የህክምና ጉዳዮች ዋና አማካሪ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ የሙከራው ውጤት “መልካም ዜና” መሆኑን ገልጸው፤ የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር የሙከራውን ውጤት የተመለከቱ መረጃዎችን እስከሚመረምረው ድረስ ጥንቃቄ እንዲደረግ አስጠንቅቀዋል።
በባለሥልጣኑ ፈቃድ ካገኘም ሞልነፒራቪር የተሰኘው ይህ መድኃኒት ኮቪድ-19ን ለማከም የዋለ የመጀመሪያው እንክብል ይሆናል።
ከዚህ ቀደም ኢንፍሉዌንዛን ለማከም ይውል የነበረው ይህ መድኃኒት በቫይረሱ የዘረ መል ሥርአት ውስጥ መዛባትን በመፍጠር በሰውነት ውስጥ እንዳይስፋፋ የሚያደርግ ነው።
- በአፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባት ግብን ያሳኩት 15 አገራት ብቻ ናቸው ተባለ
- ኮሮናቫይረስን ለማከም የሚውለው የኢቦላ መድኃኒት ህሙማንን ይፈውሳል?
- ሬምዴሲቬር፡ ሐኪሞች እያዳነቁት ያለው የኮሮናቫይረስ መድኃኒት
በ775 ሰዎች ላይ በተደረገው ሙከራም 7̄ በመቶው ብቻ ሆስፒታል ገብተው ሲታከሙ፤ እንክብሉን ያልወሰዱት ደግሞ 14.1 በመቶው ተኝተው ለመታከም ሆስፒታል ገብተዋል።
መድኃኒቱ ካልተሰጣቸው ሰዎች ቡድን ውስጥ ደግሞ ስምንት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሲሞቱ ሞልነፒራቪር ከወሰደው ቡድን ውስጥ ግን አንድም ሰው አልሞተም።
ጥናቱ ገና በሌሎች ምሁራን አልተገመገመም፤ ነገር ግን መድኃኒቱ ቫይረሱ ራሱን ለማባዛት የሚያመነጨው ኢንዛይም ላይ በማነጣጠር የሚሰራ ነው ተብሏል። ይህም መድኃኒቱ በአዳዲስ የኮቪድ ዝርያዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤታማነት እንዲኖረው ያደርጋል ብሏል አምራቹ መርክ።
“እንዲህ ያሉ ፀረ ቫይረስ ህክምናዎች በተለይም ላልተከተቡ ሰዎች እና ሰውነታቸው ለክትባት ምላሽ ለማይሰጥ ሰዎች ጥቅሙ ከፍ ያለ ሲሆን ይህም ወረርሽኙን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” ሲሉ የመርክ የተላላፊ በሽታዎች ምክትል ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መድኃኒቱ አንድ ሰው ኮቪድ እንደያዘው በፍጥነት መወሰድ እንዳለበት ጥናቱ ያመለከተ ሲሆን፤ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ መድኃኒቱን የወሰዱ ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት ውጤቱ ያነሰ በመሆኑ መድኃኒቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
መርክ ይህንን ኪኒን ለኮቪድ ሕክምና እንዲውል የመጀመሪያውን ሙከራ ያካሄደ ተቋም ነው፤ ነገር ግን ሌሎች ድርጅቶችም በተመሳሳይ ሕክምና ላይ እየሰሩ ነው።
በአሜሪካ ተቀናቃኙ ተቋም ፋይዘር በሁለት ፀረ ቫይረስ ኪኒኖች ላይ ሰፊ ሙከራዎችን ማካሄድ ጀምሯል። ሮቼ የተሰኘው የስዊስ ድርጅትም ተመሳሳይ ሙከራዎችን እያካሄደ ነው።
መርክ እስከ እ.ኤ.አ. 2021 መጨረሻ ድረስ 10 ሚሊዮን የሚደረሱ የሞልነፒራቪር እንክብሎችም ለማምረት እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ መድኃኒቱ በተቆጣጣሪ አካሉ ፈቃድ የሚያገኝ ከሆነ የአሜሪካ መንግሥት የአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኪኒኖችን ለመግዛት መስማማቱም ታውቋል።
የመድኃኒት አምራቹ ከሌሎች አገራት ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን ለማድረግ እየሰራ ሲሆን ኪኒኖቹን ለታዳጊ አገራት ከሚያመርቱ ተቋማት ጋርም ፈቃድ የመስጠት ድርድር እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
በርካታ ምሁራንም ይህ መድኃኒት ፈቃድ የሚያገኝ ከሆነ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።