4 ጥቅምት 2021, 13:12 EAT

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መንግሥት በዚህ ዓመት ትኩረት በሚያደርግባቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ንግግር አድርገዋል።
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት የሥራ ዘመኑን ሲጀምር፣ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም ቀጣይ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎችን አመልክተዋል።
“ጠንከራ ፓርላማ ለመልካም አስተዳደር” ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ በፓርላማው የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፤ ተከራክረው የሚያሸንፉበት ቦታ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቷ ሲወሰዱ የነበሩ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች፤ ኢኮኖሚው ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ በመታደግ እና በማነቃቃት ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በ2014 በጀት ዓመት የመንግስት ገቢን 600 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማድረስ መታቀዱንና፤ ከዚህም ውስጥ 83 በመቶው የሚሆነው ገቢ በታክስ እንደሚሰበሰብ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለፀዋል።
ጠቅላላ የሸቀጦች ንግድ ገቢም 5 ነጥብ 25 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
- ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ማን ናቸው?
- ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ታወቀ
- ዛሬ የሚመሰረተው አዲሱ መንግሥት ከከዚህ ቀደሞቹ በምን ይለያል?
ሆኖም ግን የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት የምጣኔ ሀብቱ ዋነኛ ፈተናዎች ሆነው መቀጠላቸውን እና የመንግሥት ዋነኛ የምጣኔ ሀብት ትኩረት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
“ማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ይቀጥላሉ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋፋት፣ የዋጋ ግሽበት በመቀነስ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች የገጠሙ ጉድለቶችን በማረም ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።”
እየጨመረ ለመጣው የዋጋ ግሽበት መንስኤ የሆኑ የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ ዝናብን መሰረት ያደረገ የግብርና ሥርዓት፣ የተዛባ ንግድ ሥርዓት ለማስተካከል በትኩረት ይሰራል ሲሉም አክለዋል።
የገንዘብ እና ፊስካል ፖሊስ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም ገልፀዋል።
የአረንጓዴ አሻራ
መንግሥት በቀጣይ ዓመት የደን ሀብት ቁጥርን ለመጨመር ስለማቀዱ ፕሬዝዳንቷ አመላክተዋል።
በአራት ዓመት 20 ቢሊዮን ዛፎች ለመትከል የተያዘውን እቅድ በማሳካት የሕዝቡን የምግብ ዋስትና ማረጋጋጥ ይገባል ብለዋል።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የሥራ እድል እንዲፈጠር በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ከፍተኛ ማዕድን በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች እንዲቀረፉ በልዩ ትኩረት ይሰራል ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ለባህላዊ እና አነስተኛ ማዕድን አምራቾችም ልዩ ትኩረት ይሰጣል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮንስትራክሽን
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አቅም በመገንባት አብዛኛው የአገር ውስጥ ፍላጎት በአገር በቀል ኩባንያዎች እንዲሸፈን እንደሚደረግ የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ፣ “ኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ከፍተኛ የሥራ እድል ይፈጥራል “ብለዋል።
ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን እና አዳዲስ መዳረሻዎች እንዲለሙ ይደረጋል። በገበታ ለአገር የተጀመሩ ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ የቱሪስት መዳረሻዎች በእቅዳቸው መሰረት ይከናወናሉ ሲሉም ገልፀዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተጠናቀቀው ዓመት ተከናውኖ እንደነበረ ያስታወሱት ፕሬዝዳንቷ፤ የውሃው ሙሌት እንዳይከናወን ዓለም አቀፍ ጫናዎች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ሕዳሴ ግድብ በተያዘው ዓመት “ብርሃን ይሆናል” ብለዋል ፕሬዝደንቷ።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ስድስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የሁለቱን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎቻቸውን የመረጡ ሲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በተመሰረተው ምክር ቤት አማካይነት ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን እንዲመሩ ተመርጠው ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።