4 ጥቅምት 2021, 18:06 EAT

በመስቀል አደባባይ የአዲስ መንግሥት ምስረታና በዓለ ሲመት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ሁሉን አካታች ውይይት እንደሚካሄድ አመለከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ተወካዩት በታደሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ ብሩህ ለማድረግ “በመንግሥታችን እና በፓርቲያችን ስም ቃል እገባለሁ” ብለዋል።
በበዓለ ሲመታቸው ላይ በመስቀል አደባባይ ለታደመው ሕዝብ እና የተለያዩ አገራት መሪዎች ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ለኢትዮጵያ ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉ እንዲሁም አገሪቱን ያለመታከት የሚያገለግሉ እናትና አባቶች “አደራ አለብን” ብለዋል።
ጨምረውም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በእሳቸው መሪነት የመንግሥት ሥልጣንን የተረከበው አመራር ሌብነትን የሚጠየፍ፣ በቅንነት የሚያገለግል እና ሕዝብን ሳይለያይ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ የሚሠራ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናትና አይበገሬነት “ከዚህ ሕዝብ በመፈጠሬ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል” ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ ተደምጠዋል።
ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተፈለገውን ያህል ከእንከን የጸዳ እንዳልሆነ ጠቁመው “ቢሆንም ግን አንድ እርምጃ ወደፊት አራምዶናል” ብለዋል።
“ኢትዮጵያን እንደ ሕዝብ በአንድነት ያሸነፍንበት ምርጫ ነው” በማለት የሰኔውን ምርጫ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸውታል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሸናፊ ብቻውን የሚገንበት ሳይሆን የመግባባትና በጋራ የመሥራት እንደሚሆን በንግግራቸው ጠቁመዋል።
በቀጣይም ሁሉን አካታች የሆነ ብሔራዊ ውይይት እንደሚካሄድና ይህም ሕብረ ብሔራዊነት የሚረጋገጥበት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚንስትርነት ቃለ መሐላ የፈጸሙት ዐቢይ አሕመድ “በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት በምንመሠርትበት ቀን ከፊታችሁ በመቆሜ ፈጣሪን አመሰግናለሁ” ሲሉ ስለ ምርጫው ውጤት እንዲሁም ስለ ፓርቲያቸው ተናግረዋል።
“ሥልጣን በሴራ ሳይሆን በእውነተኛ የሕዝብ ድምጽ የሚመነጭ በማድረግ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት አረጋግጠናል” በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዳደራቸውን ገልጸውታል።
አያይዘውም “የፖለቲካ ሥርዓቱ የአሸናፊ ሳይሆን የመግባባት እንዲሆን አብረን እንሠራለን። በንግግር እና በምክክር ለአንገብጋቢ ችግሮች መፍትሔ እናገኛለን። አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን። ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙርያ የምንፈታበት ይሆናል” ብለዋል።
በቀጠናው ሕዝብን ከሚያለያይ ይልቅ አንድ የሚያደርግ ገመድ እንዳለ ጠቁመው፤ በቀጠናው ያለውን የተበታተነ አቅም አሰባስቦ ወደ ትልቅ ደረጃ መሻገር እንደሚቻል ለጎረቤት አገሮች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመስቀል አደባባይ ባደረጉት ንግግር፤ ከእስልምናና ከክርስትና ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲሁም ቀደምት ታሪክን አጣቅሰው ኢትዮጵያን “መርከቧ ኢትዮጵያ የፍትሕ የነጻነት የእኩልነት ተምሳሌት ናት” ሲሉ አሞግሰዋል።
ሕዝቡንም “ድንቅ ሕዝቦች ነን” ሲሉ ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የዋጋ ንረትን መግታት እንደሚሆን እንዲሁም ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንደሚጠናቀቅም ቃል ገብተዋል።
እሳቸው የሚመሩት አስተዳደር “የሚያስብ፣ የሚያቅድ፣ የሚከውን እንጂ ህልመኛ ብቻ ሊሆን አይገባም” ብለውም አመራራቸው ውጥኑን ከግብ የሚያደርስ እንደሚሆን አመልክተዋል።
አስተዳደሩ ሁሌም እንከን የለሽ እንደማይሆን ጠቁመው፤ መጪው ትውልድ ስህተታቸውን እያረመ እንደሚዘልቅ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ “በቀጣይ ዓመታት ፈታኞቻችንን አሸንፈን አገራችንን በብልጽግና ጎዳና እናስኬዳለን” ያሉ ሲሆን፤ ንግግራቸውን ሲያገባድዱ ከታዳሚዎቹ መካከል ‘ዐቢይ፣ ዐቢይ፣ ዐቢይ’ በሚል የድጋፍ ድምጽ የሚያሰሙ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመሪነት መንበሩን በይፋ ከተረከቡ በኋላ ነገ ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚኒስትሮቻቸውን አቅርበው እንዲሾሙላቸው ያደርጋሉ።
ዛሬ የተካሄደው የመንግሥት ምስረታና ሲመተ በዓል ባለፉት 30 ዓመታት ከታዩት የተለየ ሲሆን ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ተገኝተውበታል።