11 ጥቅምት 2021, 10:57 EAT

ከሠላሳ አራት ዓመት ገደማ በፊት የወቅቱ የቡርኪናፋሶ ፕሬዝዳንት ቶማስ ሳንካራ አስደንጋጭ ግድያ የተፈጸመበት። እነሆ አሁን ከ34 ዓመት በኋላ “የአፍሪካው ቼ ጉቬራ” በመባል በሚታወቀው ሰው ግድያ ተባባሪ በመሆን 14 ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ቀርቡ።
የባለግርማ ሞገሱ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ እአአ ጥቅምት 15/1987 በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት በወታደሮቹ ነበር በጥይት ተገደለው። ይህን ተከትሎ የቅርብ ጓደኛው ብሌዝ ኮምፓዎሬ ወደ ሥልጣን መጣ።
ከግድያው ከአራት ዓመት ቀድም ብሎ ሳንካራና ካምፓዎሬ ሳንካራን ፕሬዝዳንትነት ያበቃውን መፈንቅለ መንግሥት መርተዋል።
ኮምፓዎሬም ከ14ቱ ተከሳሾች መካከል ነበር። በጎረቤት አይቮሪ ኮስት በግዞት የሚገኘው ኮምፓዎሬ እአአ በ2014 በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሥልጣኑን ለቆ ነው የተሰደደው። ነገር ግን በሳንካራ ግድያ ውስጥ እጁ እንደሌለበት በተደጋጋሚ አስተባብሏል። በፍርድ ሂደቱ እንደማይገኝም አስታውቋል።
ምንም እንኳን ጊዜው ቢቆይም ሳንካራ በመላው አፍሪካ እንደ ተምሳሌት ሆኖ ይታያል። በምዕራብ አፍሪካ ታክሲዎችን በምስሉ ያስጌጣሉ። የደቡብ አፍሪካው የተቃዋሚ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ከምሳሌዎቹ አንዱ አድርጎ ሳንከራን ይጠቅሳል።
ሳንካራ ለምን እንደ ጀግና ይታያል?
የቶማስ ሳንካራ የመታሰቢያ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ሉክ ዳሚባ “ለእኛ ሳንካራ ጀግናችን ነበር። ሕዝቡን ይወዳል። አገሩን ይወዳል። አፍሪካን ይወዳል። ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል” ብለዋል።
አገሪቱ በእሱ የስልጣን ዘመን ነበር ከአፐር ቮልታ ወደ ቡርኪና ፋሶ ስያሜዋን የቀየረችው። ትርጉሙ “የቀና ሰዎች ምድር” ማለት ነው።
ሳንካራ ቅንጡ የሚባል የአኗኗር ዘይቤ አልነበረውም። የራሱን እና የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ሁሉ ቀንሷል። የመንግሥት ሹፌሮችን እና አንደኛ ደረጃ የአየር መንገድ ትኬቶች እንዳይጠቀሙም አግዷል።
- አሜሪካዊያኑ ጥንዶች የኒውክሌር ምስጢሮች ሸጠዋል ተብለው ተከሰሱ
- በአውሮፓ ለመቆየት በዲግሪ ላይ ዲግሪ የሚሰበስቡት ናይጄሪያውያን ተማሪዎች
- ከአራት ዓመት በፊት ማሊ ውስጥ የታገቱት ኮሎምቢያዊት መነኩሲት ተለቀቁ
ለትምህርት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በአገሪቱ ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች በ1983 ከነበረበት 13 በመቶ በ1987 ወደ 73 በመቶ አድጓል። እንዲሁም ግዙፍ ብሔራዊ የክትባት ዘመቻን በበላይነት መርቷል።
ከፊውዳል ባለንብረቶችም መሬት በቀጥታ ለድሃ ገበሬዎች አከፋፍሏል። ይህም የስንዴ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
ተባበረችው አፍሪካ የ”ኒዮ-ቅኝ አገዛዝ” ተቋማት ብሎ ከጠራቸው እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ተቃራኒ እንድትቆም ጥሪ ያቀርብ ነበር።
አንድ ጊዜ “የሚያበላህ ይቆጣጠርሃል” ሲል መናገሩ ይጠቀሳል።
አፍሪካ ውስጥ እንደ ቡርኪና ፋሶ ባሉ በርካታ ቅኝ ግዛቶቿ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበራትን የፈረንሳይን የበላይነት የሚገዳደር የፀረ-ኢምፔሪያሊስት የውጭ ፖሊሲን ይፋ አደረገ። ፈረንሳይን እሱን ለመግደል ፊታውራሪ ነበረች ስትል ባለቤቱ ማሪያም ትከሳለች።
በኡጋዱጉ የሚገኘው የቶማስ ሳንካራ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው “እሱ ፕሬዝዳንቴ ሆኖ ይኖራል። ለሕዝቡ ያደረገው ነገር እኛ ወጣቶች እሱ ያደረገውን እንድናደርግ ያበረታታናል” ብሏል።
በዋና ከተማዋ ኡጋዱጉ በሚገኘው ቶማስ ሳንካራ የመታሰቢያ ፓርክ ውስጥ ስድስት ሜትር ርዝማኔ ያለው የነሐስ ሐውልት እ.ኤ.አ. በ2019 ይፋ ተደርጓል። የመጀመሪያው ሐውልት ላይ ቅሬታዎች በመነሳታቸው ባለፈው ዓመት በድጋሚ ተሠርቷል።
ዳሚባ እንዳሉት ፓርኩን ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዟል። ኦዋጋዱጉን ወደታች የሚመለከት 87 ሜትር ከፍታ ያለው ማማ ደግሞ አንዱ ነው።
ለሳንካራ መቃብር ቤት፣ የሲኒማ አዳራሽ እና በስሙ የተሰየመ የሚዲያ ቤተ መጽሐፍትም ይኖራል። እነዚህ ማስታወሻዎች የሳንካራን አብዮታዊ ሃሳቦች ለትውልድ ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተቺዎቹስ?
የሳንካራ አክራሪ የግራ ክንፍ ፖሊሲዎች በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተተችቷል።
እአአ በ 1986 አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታስረው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል።
በሳንካራ መንግሥት ውስጥ የመረጃ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ሰርጌ ቴኦፊል ባልማ “የብዝሃነት ዴሞክራሲ ሃሳብን ለመቀበል በጣም የዘገየ ይመስለኛል። ተቃዋሚዎቹን ለማናገርና እና ሊያዳምጣቸው አልቻለም” ብለዋል።
ፕሮፌሰር ባሊማ አክለውም “ለሕዝብ ሥልጣን መስጠት ስለፈለገ የሕዝቡን ግላዊና ሕዝባዊ የህይወት ዘይቤ በተገቢው መንገድ ለመምራት ለተመለመሉት የአብዮቱ መከላከያ ኮሚቴዎችን [ሲዲአር] ለሚመሩት ሠርቶ አደሮች ሥልጣን ሰጠ። በእውነቱ እነሱም የእሱን ሥልጣን ያጠለሹ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ተገኝተዋል።”
እአአ በ 2020 ከአፍሪካ ሪፖርት ድርገጽ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት እና በሳንካራ ከስልጣን የተባረሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዣን-ባፕቲስት ኦውድራጎ “በግል ፍላጎት እና የፖለቲካ ማኪያቬሊያኒዝም” በባህሪው ውስጥ ቦታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የፍርድ ሂደቱ ለምን ረዥም ጊዜ ፈጀ?
ወንድሙ ፖል ሳንካራ “የ27 ዓመታቱ የብሌዝ ኮምፓዎሬ አገዛዝ ተጨምሮበት ረዥም ጊዜን ጠብቀናል። በእሱ አገዛዝ ዘመን ፍርድ አለ ብለን እንኳን ማለም አልቻልንም” ብሏል።
ሚስቱ ስለባለቤቷ ግድያ እአአ በ1997 የወንጀል ቅሬታ ብታቀርብም ምርመራው ሊቀጥል ይችላል የሚለውን ለመወሰን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 15 ዓመት ፈጅቶበታል።
ሆኖም ኮምፓዎሬ እአአ በ2014 ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ ብዙም ፈቀቅ አላለም ነበር።
በቀጣዩ ዓመት የእሱ ነው የተባለ አስከሬን ተቆፍሮ ቢወጣም በዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራ የእሱ መሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም።
እአአ በ2016 የቡርኪናፋሶ ባለሥልጣናት የፈረንሳይ መንግሥት ስለ ሳንካራ ግድያ ያለውን ወታደራዊ ሰነዶችን እንዲለቅን በይፋ ጠይቀዋል።
እነዚያ ሰነዶች በሦስት ደረጃ ወደ ቡርኪና ፋሶ ተዛውረዋል። የመጨረሻው ኦጋዱጉ የደረሰው እአአ ሚያዝያ 2021 ነው።

በፍርድ ሂደቱ ላይ ሌላ ማን ይቀርባል?
የኮምፓዎሬ የቀድሞው አዛዥ ጄኔራል ጊልበርት ዲንዴሬ እና ሌሎች 11 ሰዎች በወታደራዊው ፍርድ ቤት እንደሚገኙ ይጠበቃል። “የመንግሥትን ደኅንነት በማጥቃት”፣ “በግድያ ተባባሪነት” እና “አስከሬን በመደበቅ” ክስ ይቀርብባቸዋል።
እአአ በ2015 ባልተሳካው መፈንቅለ መንግሥት ሚና ነበረው በሚል ዲንዴሬ 20 ዓመት ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛል።
ከተከሳሾቹ መካከል የሞት የምስክር ወረቀቱን የፈረመው ዶክተር ዲቤሬ ዣን ክሪስቶፍ ይገኝበታል። ሐኪሙ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በተፈጥሯዊ ምክንያቶች ሞተዋል ሲል ፈርሟል። ሐኪሙ የሕዝብ ሰነድ በማጭበርበር ክስ ቀርቦበታል።
በሌለበት የሚከሰሰው የኮምፓዎሬ የቀድሞ የደኅንነት ኃላፊ ሂያሲን ካፋንዶ ነው። ዓለም አቀፉ የእስራት ማዘዣ ወጥቶበታል። ሳንካራን እና ሌሎች 12 ሰዎችን የገደለውን ቡድን በመምራት ክስ ተመስርቶበታል።
የፍርድ ሂደቱ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?
ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግሥት ቡድን ጋር የተቆራኙ የጂሃዲስት ቡድኖች የሚያደርሱባትን ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየታገለች ያለችው ቡርኪና ፋሶ የፍርድ ሂደቱ የበለጠ እንዳትረጋጋ ሊያደርጋት ይችላል የሚል ሥጋት አለ።
ኮምፓዎሬ አሁንም በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው ሲሆን የእሱ ታማኝ የሆኑ የወታደር ክፍሎች ችግር ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ አንዳንድ ተንታኞች አስጠንቅቀዋል።
ይህ ስለመሆኑ ግን ትንሽ ምልክት ነው ያለው።
በተቃራኒው ፕሬዝዳንት ሮች ማርክ ካቦሬ የፍርድ ሂደቱ ውጥረትን አቃሎ ብሔራዊ ዕርቅን ያጠናክራል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
በኢንተርናሽናል ክራይወሲስ ግሩፕ የሳህል ተንታኝ የሆነው ማቲው ፔሌሪን “እንዲህ ዓይነቱ ፍርድ አለመረጋጋትን ሊያዳብር ይችላል ብዬ አላምንም” ሲል እአአ በ2020 ለፈረንሳዩ መጽሔት ጁን አፍሪክ ተናግሯል።
አክሎም “ያለ ፍትህ ዕርቅ እምብዛም አይገኝም” ብሏል።