19 ጥቅምት 2021, 15:22 EAT

የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት በአገሪቱ በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ ያለ ነው ባሉት የዴልታ አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ ላይ የቅርብ ክትትል እያደረጉ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዴልታ የተባለው የኮቪድ-19 ዝርያ ቀዳሚው የቫይረሱ አይነት ሲሆን፤ ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ውቅት ከሚመዘገቡት የበሽታው ዝርያዎች መካከል 6 በመቶው አዲሱ አይነት እንደሆነ ነው።
ኤዋይ.4.2 የሚባለውና አንዳንዶች “ዴልታ ፕላስ” የሚሉት ይህ አዲስ የቫይረሱ አይነት ከፍ ያለ በሕይወት የመቆየት ዕድል ሳይኖረው አይቀርም ተብሏል።
ይህ የቫይረስ ዝርያ ምን ያህል አስጊ ሊሆን እንደሚችል ሙከራዎች እየተደረጉ ነው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን አሁን በሽታውን ለመከላከል ከሚሰጡት ክትባቶች አቅም በላይ ሊሆን የሚችልበት ዕድል የለውም።
ይህ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አለ የተባለው የቫይረሱ አዲስ ዝርያ አሳሳቢ መሆን አለመሆኑ ገና ያልተለየ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሌሎቹ በተለየ ስለሚያስከትለው ጉዳትም የተባለ ነገር የለም።
አዲስ የተባለው ዝርያ ምንድን ነው?
በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፤ ሁልጊዜም ቫይረሶች ባህሪያቸውን ስለሚቀይሩ አዲስ አይነት የቫይረስ ዝርያ ማግኘት የሚያስደንቅ አይደለም።
ቀዳሚው የዴልታ ቫይረስ ባለፈው ግንቦት ወር በዩናይትድ ኪንግደም ሲገኝ ኣሳሳቢ ዝርያ ተብሎ ተለይቶ ነበር። በአገሪቱ ቀደም ሲል የተከሰተውና በስፋት ተሰራጭቶ የነበረው አልፋ የተባለው ዝርያ ነው።
ነገር ግን በሐምሌ ወር ላይ አዲስ ነው የተባለውን ኤዋይ.4.2 የቫይረሱን ዝርያ ለዩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዚህ ቫይረስ ስርጭት በጣም ዘገምተኛ የነበረ ሲሆን በለውጥ ውስጥ አልፏል።
እስካሁን ቫይረሱ ባለፈበት የለውጥ ሂደት ምክንያት ከሌሎቹ በበለጠ ተላላፊ መሆኑን የሚያመለክት ነገር የለም። ባለሙያዎችም ይህንን ለማወቅ ጥናት እያደረጉ ነው።
አዲሱ የዝርያ አይነት ከዩኬ ባሻገር በተወሰኑ ህሙማን ላይ አሜሪካ ውስጥ የታየ ሲሆን ዴንማርክ ውስጥ የተመዘገበው ክስተት እየቀነሰ ነው።