19 ጥቅምት 2021, 07:02 EAT

የመሬት ምስል

በሰው ልጅ ድርጊት ምክንያት የምድራችን ሙቀት መጠን ከቀን ቀን እየጨመረ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ደግሞ የእያንዳንችንን ሕይወት እየቀየረው ይገኛል።

በየቦታው ድርቅ እየታየ ነው፤ የውቅያኖሶች መጠን ጨምሯል፤ በርካታ ነብሳት ከምድራችን እየጠፉ ነው።

ከፊት ለፊታችን ያለው ፈተና ከባድ ቢሆንም መፍትሄዎች ግን አሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ ምንድነው?

የአየር ንብረት ማለት በአንድ ሥፍራ ያለው የአየር ፀባይ በዓመታት የሚያሳየው አማካይ ውጤት ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የዚህ አማካይ አየር ፀባይ መቀየር ማለት ነው።

በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ከዚህ በፊት ከዓመት ዓመት ብናኝ በረዶ ያስተናግድ የነበረ ሥፍራ፣ ከዓመታት በኋላ ይህ ተቀይሮ ከፊል ፀሐያማ መሆን ሲጀምር የአየር ንብረት ለውጥ ተስተዋለ ማለት ነው።

የአየር ንብረቱ በፍጥነት እየተለዋወጠ ያለበት ምክንያት የሰው ልጅ ነው።

የሰው ልጅ ነዳጅ ይጠቀማል፤ ጋዝና ከሰል ያቀጣጥላል፤ በድንጋይ ከሰልና በጋዝ ለቤቱ ብርሃን ያጎናፅፋል፤ ፋብሪካ ያንቀሳቅሳል፤ መጓጓዣ ያበጃል።

እነዚህ ኃይል አመንጪ ንጥሮች የሚለቁት ጭስ ግሪንሃውስ ጋዝ ይባላል። አብዛኛው ክፍሉ ካርበን ዳይኦክሳይድ [CO2] ነው። ይህ ጋዝ ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት አምቆ የፕላኔታችን የሙቀት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።

ዓለማችን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1.2 ድግሪ ሴልሺዬስ ጨምራለች። ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን ደግሞ 50 በመቶ ጨምሯል።

የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት ማድረግ ያለብን የሙቀት መጠንን መቀነስ ነው ይላሉ ሳይንቲስቶች። እንደነሱ ከሆነ የምድራችን ሙቀት መጠን በ2100 ባለበት 1.5 ድግሪ ሴልሺዬስ መቆየት አለበት።

ነገር ግን አሁን እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ የምድራችን ሙቀት መጠን በያዝነው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ወደ 2 ድግሪ ሴልሺዬስ ከፍ ሊል ይችላል።

ሳይንቲስቶች ይህ ብቻ አይደለም አስጊው ነገር ይላሉ። የሙቀት መጠኑ ወደ 4 ዲ.ሴ. ከፍ ሊልም ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ አስከፊ ሙቀት ተከስቶ ሚሊዮኖች በውሃ መጠን መጨመር ምክንያት ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ፤ እፅዋትና እንስሳት ከምድራችን ይጠፋሉ።

በውሃ የተጥለቀለቀ ጎዳና

የአየር ንብረት ለውጥ መዘዙ ምንድነው?

የከረረ የአየር ፀባይ የሰዎችንና የተፈጥሮ ሃብትን ኅልውና እየተገዳደረው ይገኛል።

በዚህ ከዕለት ተዕለት እየጨመረ ባለው የሙቀት መጨመር ምክንያት አንዳንድ ሥፍራዎች ወደ በረሃነት እየተቀየሩ ነው።

በሌላ በኩል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ከፍተኛ የዝናብ መጠን አጋጥሟቸዋል። ይህ ደግሞ ለጎርፍ ያጋልጣል።

ይሄ በቻይና፣ ጀርመን፣ ቤልጂዬምና ኔዘርላንድስ በቅርብ ጊዜያት ያየነው ክስተት ነው።

ምጣኔ ኃብታቸው ያላደገ ሃገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ይቸገራሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመፋለም የሚያስችል የገንዘብ አቅም አለመኖር ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ እጅግ ተጠቂ ከሚሆኑ የምድራችን ክፍሎች አንዱ ውቅያኖስ ነው። የሙቀት መጠኑ መጨመር ለሰደድ እሣት አንዱ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

እንደ ሳይቤሪያ ያሉ ግግር በረዷማ ሥፍራዎች ሲቀልጡ፣ ታምቀው የቆዩ ግሪንሃውስ ጋዞች ይለቀቁና የአየር ንብረቱን የበለጠ ያወሳሱባታል።

ዓለማችን ሞቃታማ ስትሆን እንስሳት ምግብ ፈልጎ መብላትና ውሃ መጠጣት እየከበዳቸው ይመጣል። ለምሳሌ በረዷማ አካባቢ የሚኖሩ ድቦች በረዶው ሲቀልጥ ሊጠፉ ይችላሉ። ዝሆኖች ደግሞ በቀን የሚያስፈልጋቸውን ከ150-300 ሊትር ውሃ አያገኙም ማለት ነው።

ሳይንቲስቶች ችግሩን ለመግታት እርምጃ ካልተወሰደ እስከ 550 ዝርያዎች በያዝነው ክፍለ ዘመን ሊጠፉ ይችላሉ ባይ ናቸው።

የዓለም ምስል

የተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ የሚደርሰው አደጋ

የአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተለያዩ አደጋዎችን ነው ይዞ የሚመጣው። አንዳንድ ሥፍራዎች ከበፊቱ የበለጠ ሙቀት ያጠቃቸዋል፤ ሌሎች ሥፍራዎች ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ ያስተናግዳሉ። የተቀሩት ደግሞ ድርቅ ያጠቃቸዋል።

ድብ

መንግሥታት ምን እያደረጉ ነው?

በፈረንጆቹ 2015 ፓሪስ ላይ ሃገራት አንድ ላይ ተባብረው ከሠሩ የሙቀት መጠኑ ከ1.5 ሴልሺዬስ በላይ እንዳይሆን ማድረግ እንሚቻል የሚያትት ስምምነት ፈርመዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ሃገራት የካርበን ልቀት መጠን እስከ 2030 ባለው ጊዜ እንዴት ሊቀንሱ እንዳሰቡ የሚወያዩበት መድረክ በወርሃ ኅዳር ታዘጋጃለች።

በርካታ ሃገራት በ2050 የካርበን ልቀት መጠኑን ዜሮ ለማድረግ ተስማምተዋል። ባለሙያዎች ይህ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ነው ይላሉ። ነገር ግን መንግሥታት፣ ቢዝነሶች እንዲሁም ግለሰቦች አንድ ላይ ካልሠሩ ዋጋ የለውም ይላሉ።