October 23, 2021  

የተባበሩት መንግሥታት አውሮፕላን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ የሚያደርጋቸውን ሁሉንም የሰብአዊ እርዳታ በረራዎችን ከአርብ ጀምሮ ማቋረጡን አስታወቀ።

አርብ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም ወደ መቀለ የተጓዘው አውሮፕላን ማረፍ ሳይችል ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ነው የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ በረራዎች እንዲቆሙ መደረጋቸውን የገለጹት።

አርብ ረፋድ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለአራተኛ ቀን በመቀለ የአየር ጥቃት የፈጸመ ሲሆን በዚህም የህወሓት ወታደራዊ ማሰልጠኛ እና የወታደራዊ መገናኛ እንዲሁም ማዘዣ ማዕከል ነበር ያለው ስፍራ የጥቃቱ ኢላማ እንደነበር መንግሥት ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ወደ መቀለ የሚደረጉ በረራዎችን ከማገዱ በፊት አርብ ዕለት 11 መንገደኞችን የያዘ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ተነስቶ ቢሄድም እንዳያርፍ በመከልከሉ ወደ መጣበት መመለሱን ቃል አቀባዩ ስቴፋን ዱጃሪክ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

Tweet

Amanda Price

@amandaruthprice

#Ethiopia: #UN confirms that UN humanitarian flight

from Addis Ababa forced to turn back after airstrikes

began in #Mekelle on Friday. “I can confirm that the

government was informed of that flight,” the head of

@UNOCHA Southern & Eastern Africa, Gemma Connell,

told journalists.

12:18 PM · Oct 22, 2021 ·TweetDeck

727 Retweets 89 Quote Tweets 605 Likes

የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የተባለው በረራ ከአዲስ አበባ ሲነሳ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም “ከመቀለ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መቆጣጣሪያ ማማ እንዳያርፍ መመሪያ ተሰጥቶታል” ብለዋል ዱጃሪክ።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም እንዳያርፍ የተከለከለው የመንግሥታቱ ድርጅት አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ማረፉን አመልክተው ምን እንደተከሰተ “በጥንቃቄ ይመረመራል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) እንደተናገሩት የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረራ በአካባቢው እንደነበር እንደሚያውቁ ገልጸው፤ ነገር ግን የድርጅቱ እና ወታደራዊ በረራዎቹ “የተለያየ ጊዜና አቅጣጫ ላይ ነበሩ” ብለዋል።

አርብ ዕለት የተፈጸመው የአየር ጥቃትን በፈጸሙትና በመንግሥታቱ ድርጅት አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ሁኔታን በተመለከተ ግልጽ መረጃ እንደሌለ ኤፒ ዘግቧል።

የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ከአየር ጥቃቱ በኋላ ባሰፈሩት አስተያየት የመንግሥታቱ ድርጅት አውሮፕላን በሚበርበት ጊዜ ጥቃቱ የተፈጸመው አውሮፕላኑን ለማሳሳቻነት ለመጠቀምና በፀረ አውሮፕላን እንዲመታ ለማድረግ የታቀደ ነው ሲሉ ከሰዋል።

Thread

Getachew K Reda

@reda_getachew

#AbiyAhmed’s Air Force did once again strike non-

military targets around #MU campus. While this is not

outrageous enough, a #UN Aircraft had to abort its

landing because of the air strike. Our air defense units

knew the UN plane was scheduled to land & it was due

in large measure

11:04 AM · Oct 22, 2021 ·Twitter for iPhone

2,009 Retweets 181 Quote Tweets 2,005 Likes

ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር በኋላ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አማራና አፋር ክልል መስፋፋቱን ተከትሎ ሰብአዊ አርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ማቅረብ አስቸጋሪ ሆኗል የሚለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል።

በተጨማሪም በአውሮፕላን እርዳታ በአዲስ አበባ በኩል ወደ ክልሉ እንዲገባ እያደረገ ቢሆንም አሁን በረራው እንዲቋረጥ መደረጉ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ጫናን እንደሚያስከትል ተነግሯል።

አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት በአሁኑ ጊዜ በአማራና በአፋር ክሎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ሲሆን ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ የፌደራል መንግሥቱ አየር ኃይል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መቀለ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ኢላማዎች ላይ ፈጽሟል።