23 ጥቅምት 2021, 09:08 EAT

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ ተመራማሪዎች በአዲስ መልክ እራሱን የቀየረው ‘ዴልታ ፕላስ’ የተሰኘው አዲሱ የኮሮረናቫይረስ ዝርያ ከሌሎቹ በፈጠነ መንገድ ከሰዎች ወደ ሰዎች የመተላለፍ አቅም እንዳለው ገለጹ።
የዩኬ ጤና ደኅንነት ኤጀንሲ በበኩሉ ይህን አዲስ የቫይረስ አይነት “ምርምር ከሚደረግባቸው የቫይረስ አይነቶች” ዝርዝር ውስጥ ያስገባው ሲሆን ይህም ምን ያህል አስጊ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ ከባድ የሆነ የጤና ቀውስ ስለማስከተሉ ምንም የተገኘ ማስረጃ የለም።
በተጨማሪም ተመራማሪዎች ይህንን ዴልታ ፕላስ የተሰኛው አዲስ የቫይረስ አይነት በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉ የክትባት አይነቶች መከላከል እንደሚቻል እምነት አላቸው።
ምንም እንኳን ዴልታ የተሰኘው የቫይረስ አይነት ዩኬ ውስጥ በርካቶችን እያጠቃ ቢሆንም በዴልታ ፕላስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየጨመረ መጥቷል።
እስካሁን በተገኘ መረጃ መሰረትም በአዲሱ ዴልታ ፕላስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ስድስት በመቶ ደርሷል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በየዩናይትድ ኪንግደም የዚህ ቫይረስ አይነት የስርጭት መጠን በጣም ከፍተኛና ከሌሎች አንጻር ሲታይ በእጅጉ የፈጠነ ነው።
“ይህ አዲስ የኮሮናቫይረስ አይነት ከቅርብ ወራት ወዲህ ዩናይትድ ኪንግደም ውጥ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ከዴልታ ጋር ሲነጻጸርም የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ መሆንን አይተናል” ይላል የዩኬ ጤና ደኅንነት ኤጀንሲ።
በሌላ በኩል ግን ይህ አዲስ የኮሮረናቫይረስ ዝርያ ልክ እንደ ዴልታ ስጋት የሚፈጥሩ ቫይረሶች ዝርዝር ውስጥ እስካሁን አልገባም። ይህ ምድብ ከፍተኛውና አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሱ ቫይረሶች የሚካተቱበት ነው።
እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች መሰረት በመላው ዓለም በሺዎች የሚቆጠሩ የኮቪድ-19 የቫይረስ አይነቶች ይገኛሉ። ቫይረሶቹ ሁሌም ቢሆን ከቦታ ቦታ እራሳቸውን ይቀያይራሉ። በዚህም ምክንያት አዳዲስ የቫይረስ አይነቶችን መመልከት የተለመደ ነው።
ከቅርብ ወራት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም የታየው አዲሱ ቫይረስ ዝርያ ‘አልፋ’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
የደቡቡ አፍሪካው ‘ቤታ’ የተባለ ሲሆን በሕንድ በርካቶችን ያጠቃው የቫይረስ አይነት ደግሞ ‘ዴልታ’ ተብሎ እንደሚጠራ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
‘አልፋ’ የሚል ስያሜ ከተሰጠው የዩኬው ዝርያ በበለጠ መልኩ በቶሎ መሰራጨት የሚችል ሲሆን በዩኬ ለጨመረው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ምክንያት ነው።
በሌላ በኩል በቬትናም የተስተዋለው አዲሱ የቫይረስ አይነት በሕንድ እና በዩናይትድ ኪንግደም ከታዩት የቫይረሱ ዝርያዎች የተቀላቀለ ሲሆን በቀላሉ በአየር መተላለፍ የሚችል ነው።