ከ 5 ሰአት በፊት

ሁለት ጊዜ የኮቪድ-19 ክትባትን የወሰዱ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ እና አብረዋቸው የሚኖሩ ሰዎችንም እያስያስያዙ እንደሚገኙ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ይህንን ያሳወቁት በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ቤተሰቦች ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ናቸው።
እንደ ባለሙያዎቹ ከሆነ፤ ክትባቱን ሁለት ጊዜ የወሰዱ ሰዎች ክትባቱን ካልወሰዱ ሰዎች ባልተለየ መልኩ ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች ያስተላልፋሉ።
በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ምልክቶችን ቢያሳዩም ባያሳዩም፤ ቫይረሱን ክትባቱን ወዳልወሰዱ ሰዎች የማስተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህም ከአምስት ሰዎች ሁለቱ እንደማለት ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ። በሌላ አገላለጽ ደግሞ ቫይረሱን የማስተላለፍ ዕድላቸው 38 በመቶ ነው።
ነገር ግን ሁሉም የቤተሰብ አባላት ክትባቱን ወስደው ከሆነ ቁጥሩ የሚቀንስ ሲሆን፤ ከአራት ሰዎች አንድ ሰው ቫይረሱን ያስተላልፋል።
- ያደጉ አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትርፍ ክትባቶችን ለድሃ አገራት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ
- በአፍጋኒስታን የበረታው ረሃብ እናት ልጇን በአምስት መቶ ዶላር እንድትሸጥ አደረገ
- ኢትዮጵያ ከውጭ በሚገባ ስንዴ ላይ ጥርጣሬ ያላት ለምንድነው?
በመቶዎች ሲሰላ ደግሞ ሁለቱንም ዙር ክትባት ከወሰዱ ሰዎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ቫይረሱን ያስተላልፋሉ ማለት ነው።
የላንሴት ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ማዕከል እንደሚለው፤ ሁሉንም ሰው እንዲከተብ ማድረግ ከሰዎች ወደ ሰዎች የመተላለፍ እድሉን ስለሚቀንሰው አሁንም ክትባቱ ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው።
ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች በቫይረሱ ያለመያዝ እድላቸውን ከፍ ለማድረግ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች መከተባቸውን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውም ክትባቱን ቢወስዱ ይመረጣል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ያስጠነቅቃሉ።
ክትባቶች በኮቪድ-19 ምክንያት የሚከሰት ከፍተኛ ህመምን እና ሞትን ለማስቀረት ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ምንም ጥርጥር የለውም።
ነገር ግን የቫይረሱን ስርጭት መቀነስ ላይ አሁንም ብዙ የሚቀሩት ነገሮች አሉ። በተጨማሪ ደግሞ እንደ ዴልታ ያሉ አዳዲስ ዝርያዎች መምጣት ክትባቶቹ የታሰበላቸውን ያክል ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
በጊዜ ብዛት ደግሞ የክትባቶቹ የመከላከል አቅም እየቀነስ ስለሚመጣ ተጨማሪ ድጋፍ የሚሰጡ ክትባቶችን (ቡስተር) መውሰድ ግድ እያለ ነው።
በአሁኑ ሰዓት በተለይ በአውሮፓ አገራት ከፍተኛው የቫይረሱ ስርጭት እየተከሰተ ያለው በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ መሆኑን ተከትሎ በተቻለ መጠን ክትባቱን መውሰድ የሚችል የቤተሰብ አባል በሙሉ ቢከተብ ይመረጣል ይላሉ ባለሙያዎቹ።
እንግሊዝ ውስጥ በተሠራ አንድ ጥናት መሠረት ሁለት ጊዜ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ካልተከተቡት ጋር ሲነጻጸር በአዲሱ የዴልታ ቫይረስ የመያዝ ዕድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ እንደሆነ ተመልክቷል።
ሆኖም በቫይረሱ የተያዘ ሰው በሰውነቱ ውስጥ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅት የቫይረስ ክምችት እና የተከተበ ሰው የሚኖረው የቫይረስ ክምችት ተመሳሳይ ነው።
ለዚህም ነው ምንም እንኳን የተከተቡት ሰዎች ምንም አይነት ምልክት ባያሳዩም ወደ ሌሎች ሰዎች ግን የሚያስተላልፉት።