ከ 6 ሰአት በፊት

ሥጋ
የምስሉ መግለጫ,ሥጋ

ባለንበት ዘመን ተወዳጅ ከሆኑ ምግቦች አንዱ ሎብስተር የተባለው የዓሣ ዝርያ ነው። ይህ ምግብ እንደ ዛሬው ከቅንጡ ምግቦች ዝርዝር ውስጥ ከመካተቱ በፊት በጥንታዊ ሰዎች እምብዛም ቦታ አይሰጠውም ነበር።

ወደ 18ኛው ክፍለ ዘመን ብትሄዱ ሎብስተርን አጣጥሞ የሚበላ ይቅርና ለመብላት የሚመኝም አልነበረም።

ያኔ ሎብስተር በአሜሪካ ማረሚያ ቤቶች ለማዳበሪያነት ይውል ነበር። የባቡር ሀዲድ ግንባታ ሲጀመር ግን ሎብስተር በምግብነት ይቀርብ ጀመር። ያውም በቅንጡ የምግብ ዝርዝሮች ውስጥ ተካቶ።

ከዚያም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሎብስተር ባቡር ውስጥ ከመቅረብ ወደ ከተማ ሬስቶራንቶች ተሻገረ።

ቅንጡ የሚባሉ ምግቦች በዋጋ ውድ ናቸው። በቀላሉም አይገኙም።

የምግብ ታሪክ የሚያጠናው ፖሊ ራሰል እንደሚለው፤ በአንድ ወቅት ብዙም ውድ ያልነበሩ ምግቦች በሌላ ዘመን በዋጋ የናሩበት አጋጣሚ አለ።

ከዚህ በተቃራኒው የ’ሀብታሞች’ ብቻ ይባሉ የነበሩ የምግብ አይነቶች በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉም በታሪክ ታይቷል። ለዚህ ዋነኛ ምሳሌ ስኳር ነው ይላል በኢንዲያና ዩኒቨርስቲ የአንትሮፖሎጂ መምህሩ ሪቻርድ ዊልክ።

እንጆሪን የመሰሉ አንዳንድ የፍራፍሬ አይነቶች በዓመት ውስጥ በተወሰነ ወቅት ብቻ ይገኙ ነበር። በጊዜ ሂደት ግን ሰዎች ዓመቱን ሙሉ እንዲመገቧቸው ገበያ ላይ መቅረብ ጀምረዋል።

በኤደንብራ ዩኒቨርስቲ የምግብ ደኅንነት የሚያጠናው ፒተር አሌክሳንደር እንደሚለው፤ ዓመቱን ሙሉ ፍራፍሬ ማግኘት የሚቻልበት ዘመን ላይ መድረሳችን ‘የቅንጦት’ የሚባሉ ፍራፍሬዎችን የምናይበትን መንገድ ለውጧል።

የተፈጥሮ ዑደት ሲለዋወጥ ቅንጡ የሚባሉ ምግቦችም እየተለወጡ ይሄዳሉ።

ለምሳሌ የዓሣ ቁጥር እየቀነሰ ሲመጣ ምግቡ እየተወደደ፣ ዓሣ መብላት ቅንጦት እየሆነ ይመጣል ማለት ነው።

የዓሣ ዋጋ ሲወደድ ደግሞ ዓሣ አስጋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት ብለው በየቀኑ የሚያጠምዱትን ዓሣ ቁጥር ይጨምራሉ። ይህ ደግሞ የዓሣ ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት ይሆናል።

በግላስጎው ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ባለሙያዋ ኤስተር ፓፒስ እንደሚሉት፤ ቅንጡ የሚባሉ ምግቦች ከበዓል ወይም ከሌላም ለየት ያለ ቀን ጋር ይተሳሰራሉ።

አንድ የምግብ አይነት ቅንጡ የሚል ስም ሲሰጠው ሰዎች ምግቡን የመብላት ፍላጎታቸው ይጨምራል። ለምግቡ ከፍተኛ ገንዘብ ቢጠየቁም እንኳን ከመመገብ ወደኋላ አይሉም።

ቅንጡ ማዕድ ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች ጋር መቋደስ ሐሴት ይሰጣል። ይህን ስሜት የሚመዘግበው አእምሮም ቅንጡ ምግቦችን ከወዳጅ ዘመድ ጋር አስተሳስሮ ያስባቸዋል።

ቸኮሌት
የምስሉ መግለጫ,ቸኮሌት

በቀጣይ ዓመታት በጣም ይወደዳሉ ባሉ ምግቦች የትኞቹ ናቸው?

በቀደመው ዘመን ቡና እና ቸኮሌት ቅንጡ ምግቦች ይባሉ ነበር። አሁን ግን በየመደብሩ ይገኛሉ።

በቀጣይ ዓመታት ግን ቡና እና ቸኮሌት እንደ ድሮው ቅንጡ ምግቦች ውስጥ ሊመደቡ ይችሉ ይሆናል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው። የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱ ምርቶቹን አደጋ ውስጥ ይከታቸዋል።

በጥንታዊው የማያን ስልጣኔ ዘመን ኮኮዋ እጅግ ውድ መገበያያ ነበር። የስፔን ነጋዴዎች ወደ አውሮፓ ከወሰዱት በኋላ ደግሞ በቤተ መንግሥት ተወዳጅ ምግብ ሆነ።

እአአ በ1828 ኬሚስቱ ኮንራድ ጆናስ የዱቄት ቸኮሌት ካመረተ በኋላ ምርቱ በየመደብሩ የሚገኝ ሆነ።

ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ ከመገኘቱ በፊት ብዙም የሚታወቅ አልነበረም። በጊዜ ሂደት ግን በተጓዦች እና ነጋዴዎች ዘንድ እውቅናው ናኘ።

አሁን ላይ በቀላሉ በየሱቁ የምናገኛቸው ቡና እና ቸኮሌት ምናልባትም እንደ ድሮው በቀላሉ የማይገኙ ምርቶች እንዳይሆኑ ባለሙያዎች ይሰጋሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ባለሙያዋ ሞኒካ ዙሬክ “በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቸኮሌት እና ቡና ውድ እና ቅንጡ ምግቦች ሊሆኑ ይችላሉ” ትላለች።

የዓለም ሙቀት ወደ 2 ሴንቲ ግሬድ ከፍ ሊል የሚችልበት እድል መኖሩን ተከትሎ፤ ጋና እና አይቮሪ ኮስት ቡና ማምረት ከሚቸገሩ መካከል ይጠቀሳሉ።

እአአ በ2050 ቡና አብቃይ መሬት የሚባል ቦታ በከፊል ሊጠፋም ይችላል። የላቲን አሜሪካ የቡና ምርት ደግሞ 88 በመቶ እንደሚቀንስ ይገመታል።

ቡና የዓለም አቀፍ ገበያ ትስስር መሠረት፣ የምጣኔ ሀብት ዋልታም ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ግን ይህንን እውነታ ሊቀይረው ይችላል።

አሁን ላይ የቅመማ ቅመም ምርት እየቀነሰ የመጣው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ነው። የዓለም ከፍተኛ ሙቀት ሰብል የሚያጠፉ ተዋህሲያን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲራቡ ስላደረገ ምርት እያሽቆለቆለ ይገኛል።

ማዳጋስካር ውስጥ የቫኒላ ምርት የቀነሰውም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ነው። እአአ 2017 ላይ የተነሳ አውሎ ነፋስ 30 በመቶ የቫኒላ ምርትን አውድሟል።

ያኔ የቫኒላ ከብር በላይ ተወዶ ዋጋው 600 ዶላር ገብቶ ነበር።

በሱሬይ ዩኒቨርስቲ የምግብ እና ጤና ተመራማሪዋ ሞኒክ ራትስ እንደሚሉት፤ በየዕለቱ የምናገኛችው ምግቦች በቀጣይ ዓመታት ዋጋቸው እየተወደደ መሄዱ አስጊ ነው።

ቡና
የምስሉ መግለጫ,ቡና

የሥጋ ተመጋቢዎች መቀነስ

የብዙዎች የምግብ ምርጫ እየተቀየረ ነው። ለውጡ ደግሞ ሥራ ማቆምን ይጨምራል።

ብዙዎች አትክልት ተመጋቢ እየሆኑ ሲሄዱ ሥጋ ወደ ቅንጦት ምግብ ዝርዝር ውስጥ መግባቱ አይቀርም።

የሕዝብ ቁጥር መጨመር ቅንጡ የሚባሉ የምግብ አይነቶችን ሊለውጥም ይችላል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በቀጣይ ዓመታት ሥጋ መብላት በማኅበረሰቡ ዘንድ ‘ተቀባይነት የሌለው’ ሊባል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።

በእርግጥ አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ሥጋ መመገብ በብዙ ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ስለሆነ ከሥጋ መላቀቅ ቀላል ላይሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከሥጋ ውጪ ያሉ የምግብ አማራጮች ቁጥር መጨመሩ ሥጋ ተመጋቢዎች ወደ ሌላ ምግብ እንዲሸጋገሩ ያበረታታቸው ይሆናል።

የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ሲባል ሥጋ ላይ የሚጣለውን ቀረጥ የመጨመር ፍላጎት ያላቸው አገራት አሉ።

ቀረጥ ሲጨመር የሥጋ ዋጋ ውድ ይሆናል። ሥጋ መግዛት የሚችሉ ሰዎች ቁጥር በተቃራኒው ይቀንሳል ማለት ነው።

የቀንድ ከብቶች ከጋዝ ልቀት 14.5 በመቶ ድርሻውን ይይዛሉ። ይህም 41 በመቶ የሥጋ ምርትን ይሸፍናል።

የመላው ዓለም የሥጋ ምርት የሚያስከትለው የጋዝ ልቀት ሕንድ እንደ አገር ካላት ልቀት ጋር ይመጣጠናል።

በፕሮቲን የበለጸጉ እንደ ባቄላ ያሉ ሰብሎችን ለማምረት ከሚያስፈልገው መሬት 20 እጥፍ የሚያስፈልገው ለሥጋ ምርት ነው።

በአነስተኛ ወጪ የሚመረቱ ምግቦች ዋጋቸውም አነስተኛ ነው። ነገር ግን የምግብ ምርት ወጪን ለመቀነስ ብሎ ከባቢ አየርን መጉዳት አሳሳቢ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት ይጠቁማል።

ጥናቱ “ለውሃ እና አየር ብክለት እንዲሁም ለአካባቢ ውድመት የሚዳርጉ ምግቦች ገበያ ላይ በርካሽ ዋጋ ይሸጣሉ። ይህም አስጊ ነው” ይላል።

አብዛኞቻችን የምንበላው ምግብ እና የአየር ንብረት ለውጥ መካከል ያለውን ትስስር ልብ አንልም።

ገበያ ላይ የሚቀርበው ምግብ ሲመረት ከባቢ አየርን የማይጎዳ እንዲሆን ተመራማሪዎች ተስፋ ያደርጋሉ።

በኤደንብራ ዩኒቨርስቲ የምግብ ደኅንነት የሚያጠናው ፒተር አሌክሳንደር እንደሚለው፤ ሥጋ ላይ ቀረጥ መጣል አዋጭ መንገድ ቢሆን አጨቃጫቂ መሆኑ አይቀርም። ሥጋ ላይ ቀረጥ ሲበዛ ሥጋን ለማምረት ሲባል አካባቢ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ መቀነስ ቢቻልም የሥጋ ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል።

በግላስጎው ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ባለሙያዋ ኤስተር ፓፒስ እንደሚሉት፤ “በቀጣይ ዓመታት የምግብ ዋጋ ሲወጣ የምርት ሂደቱ አካባቢ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከግምት ይገባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ መንገድ የተሻለ የሥነ ምግብ ሥርዓት መፍጠር እንችላለን።”