1 ህዳር 2021, 07:24 EAT

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሕዝቡ ‘የክት’ ጉዳዩን አቆይቶ ህወሓትን ‘ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሳሪያ እና አቅም ይዞ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝመት አለበት’ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት የህወሓት አማጺያን ኮምቦልቻን ጨምሮ የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።

በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ መዲና የሆነችውን ደሴን ተቆጣጥረናል ቢልም መንግሥት ግን ደሴ በመከላከያ እና በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ትገኛለች ማለቱ ይታወሳል።

እሁድ ዕለት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ላይ በደሴ እና ኮምቦልቻ አካባቢ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ ቅዳሜ ዕለት በደሴ የተፈጸመውን እንዲህን ሲሉ አስረድተዋል።

“በደሴ አካባቢ ጠላት አስቀድሞ ያስገባቸው ሰርጎ ገቦች እንደዚሁም ሲቪል ለብሰው ለጁንታው ኃይል የሚሰሩ ባንዳዎች . . . የመከላከያ ኃይላችን ላይ ከኋላ በመውጋት የውጊያ መዛነፍ እንዲከሰት ተደርጓል።”

“ጣፋጩን ድል እናጣጥማለን”

ጠቅላይ ሚንኒትር ዐቢይ አሕመድ እሁድ ምሽት ባወጡት መልዕክት “የመረረውን ትግል ታግለን፣ ጣፋጩን ድል እናጣጥማለን” ብለዋል።

ህወሓት ለኢትዮጵያ የመከራ ቋት መሆኑን ቀጥሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ህወሓት በአራት ግንባሮች ተኩስ ከፍቶ አገር የማፍረስ ተግባሩን ገፍቶበታል” ብለዋል።

“ሰሞኑን ያለ የሌለ ኃይሉን ወደ ወሎ ግንባር አምጥቷል። አገር ለማጥፋት የመጣ መንጋ አገር ለማዳን የተነሣን ኃይል ይረብሸው ይሆናል፣ ሊያሸንፈው ግን አይችልም።”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት የጠላትን ኃይል መከታተል ያስፈልጋል ብለዋል። “በመካከላችን ሆኖ ለጠላት የሚሠራውን የህወሐት ወኪል በንቃት መከታተል ያስፈልጋል። ለዘመናት ከጠላት ጋር የጥቅም ትስስር የፈጠሩ ሰዎች ዛሬም በጉያችን ሆነው የጠላትን ምኞት ከዳር ለማድረስ ደፋ ቀና ይላሉ። ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የጠላት ወኪሎችን ማጋለጥ ይገባል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የገጠሙን ፈተናዎች የማይታለፉ ቢምስሉም “በአንድነት በመቆም፣ በጥሞና በመደማመጥ እና ተቀናጅቶ በመንቀሳቀስ” ኢትዮጵያን ከጥቃት መከላከል ይቻላል ብለዋል።

አሁን የገጠሙን ፈተናዎች የማይታለፉ እና ውስብስብ ሊመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን ቀደምቶቻችን ካዩት መከራ የሚከብዱ አይደሉም።

“ሕዝባችን የክት ጉዳዩን ለጊዜው አቆይቶ፣ ለማጥፋት የመጣውን አሸባሪውን ህወሓት ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሣሪያና አቅም ይዞ፣ በሕጋዊ አደረጃጀት መዝመት አለበት” ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክታቸው።

አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት የቀሩት የትግራይ ጦርነት ባለፉት አራት ወራት በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን በተለይ በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ውስጥ ከባድ ውጊያዎች እተካሄዱ ነው።

የአማራ ክልል መስተዳደርም የአስቸኳይ ጊዜ በማወጅ በተለያዩ ደረጃዎች የሚኘው አመራር ሕዝቡን በማስተባር በህወሓት ኃይሎች ላይ እንዲዘምት ጥሪ አቅርቧል።