ከ 3 ሰአት በፊት

በአውሮፓ እየተባባሰ በመጣው ስርጭት ምክንያት አህጉሪቱ በድጋሚ የኮቪድ ወረርሽኝ “ማዕከል” ሆናለች ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ኃላፊ ሃንስ ክሉጅ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳሉት አህጉሪቱ በየካቲት ወር ግማሽ ሚሊዮን ተጨማሪ ሞት ልታስመዘግብ ትችላለች።
ለስርጭቱ መጨመር በበቂ ሁኔታ ክትባት አለመሰጠቱን በማንሳት ትችቱን ሰንዝሯል።
“ለኮቪድ-19 መስፋፋት ምላሽ ከመስጠት ቀድሞውኑ እንዳይከሰት ወደሚያግዙ ስልቶች መለወጥ አለብን” ብለዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በመላው አህጉሪቱ ክትባቱን የመስጠት ምጣኔው ቀንሷል። በስፔን ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ሁለቱን ዙር ክትባት ወስደዋል። ይህ ቁጥር በፈረንሳይ እና በጀርመን ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ፣ 68 በመቶ እና 66 በመቶ ላይ ይገኛል።
- በዋግ ኽምራ ዞን ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆኑን ነዋሪዎችና ኃላፊዎች ገለፁ
- ፌልትማን በኢትዮጵያን ዙሪያ ስላላቸው ምልከታ ምን አሉ?
- የጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ በኢትዮጵያ ጉዳይ ይመክራል ተባለ
- በኒጀር ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት 69 ሰዎች ተገደሉ
የአንዳንድ የመካከለኛው እና የምስራቅ አውሮፓ ሃገሮች አሃዝ ደግሞ ከዚህም ዝቅተኛ ነው። እአአ ጥቅምት 2021 ሙሉ ለሙሉ ክትባቱን የወሰዱ ሩሲያውያን 32 በመቶ ብቻ ናቸው።
ክሉጅ የማዕከላዊ እስያ ክፍልን ጨምሮ 53 ሃገሮችን በሚሸፍነው የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዞን የህዝብ ጤና እርምጃዎችን መላላትን ለበሽታው መባባስ እንደተጨማሪ ምክንያት አንስተዋል። የዓለም ጤና ድርጅት በአካባቢው እስካሁን 1.4 ሚሊዮን ሰዎች መሞታቸውን መዝግቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ቴክኒካል ኃላፊ ማሪያ ቫን ኬርክሆቭ ምንም እንኳን “በቂ የክትባት እና የመሳሪያ አቅርቦት” ቢኖርም ወረርሽኙ ባለፉት አራት ሳምንታት በመላው አውሮፓ ከ 55 በመቶ በላይ ከፍ ብሏል ብለዋል።
ባልደረባቸው ዶክተር ማይክ ሪያን የአውሮፓ ተሞክሮ “ለዓለም የማስጠንቀቂያ ደወል ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
በጀርመን ስርጭቱ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ወደ 34000 የሚጠጉ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል።
በጀርመን ያለው የኮቪድ ስርጭት በዕለት ከ 37000 የሚበልጡ ሰዎች በቫይረሱ ከሚያዙባት የዩኬ የቅርብ ጊዜ ቁጥሮች በታች ነው። የህብረተሰብ ጤና ባለሥልጣናት ግን አራተኛው ማዕበል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞት ሊያስከትል እና በጤና ስርዓቱ ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 165 ሰዎች መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው 126 ሞት ጨማሪ አሳይቷል።
የጀርመን አርኬአይ ኢንስቲትዩቱ ሎተር ዊለር ስለ አስፈሪ ቁጥሮች ተናግረዋል። “አሁን የመከላከያ እርምጃዎችን ካልወሰድን አራተኛው ማዕበል የበለጠ አደጋ ያመጣል” ብለዋል። ክትባቱን ካልወሰዱት ጀርመናውያን መካከል ከ60 በላይ ዕድሜ ያላቸው ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሲሆን እነዚሀም ለበለጠ አደጋ የተጋለጡ ናቸው።
ሃንስ ክሉጅ እንደሚሉት የቫይረሱ መጨመር በጀርመን ብቻ የተገደበ አይደለም።
ባለፈው ሳምንት የሟቾች ቁጥር በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በሩሲያ ሲሆን ከ 8,100 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። በዩክሬን ደግሞ 3800 ሰዎች ሞተዋል። ሁለቱም ሀገራት በጣም ዝቅተኛ ክትባት የሰጡ ሲሆን ዩክሬን ባለፉት 24 ሰዓታት 27377 አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አስመዝግባለች።
ሮማኒያ በ 24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነውን የ591 ሰዎችን ሞት አስመዝግባለች። በሃንጋሪ በየዕለቱ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ከእጥፍ በላይ አድጎ ባለፈው ሳምንት 6268 ደርሷል። ጭንብል መልበስ አስገዳጅ የሆነው በሕዝብ ማመላለሻዎች እና በሆስፒታሎች ብቻ ነው።
ዶክተር ሪያን “በአሁን ተጨማሪ ጥቂት ሰዎችን ከከተብን ወረርሽኙ አብቅቷል የሚል ሃሳብ ላይ ነን። ጉዳዩ እንደዚያ አይደለም” ብለው ሃገራት ቀዳዳቸውን እንዲደፍኑ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የደች መንግሥት ጭንብል መልበስ እና አካላዊ መራራቅን ህዝብ በሚሰባሰብበት ቦታዎች ላይ እንደሚጀምር በዚህ ሳምንት ተናግሯል። ምክንያቱ ያለው ደግሞ በሳምንት ውስጥ የሆስፒታል አልጋዎች የመያዝ ምጣኔ በ 31 በመቶ ከፍ በማለቱ ነው ።
የኮቪድ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ላትቪያ ከሰኞ ጀምሮ ለሦስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥታለች።
ክሮሺያ ሐሙስ ዕለት 6310 አዳዲስ በቫእረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች። ይህ ቁጥር እስካሁን ድረስ ከታየው ከፍተኛው ቁጥር ነው። ስሎቫኪያ ሁለተኛውን ከፍተኛ ቁጥር መዝግባለች። የቼክ ስርጭት በፀደይ ወቅት ወደ ነበረበት ደረጃ ተመልሷል።
የእንግሊዝ ምክትል ዋና የህክምና መኮንን ፕሮፌሰር ጆናታን ቫን ታም በበኩላቸው በጣም ብዙ ሰዎች ወረርሽኙ እንዳበቃ ያምናሉ ብለዋል።
ከፍተኛ የክትባት መጠን በደረሰባቸው ሃገሮች የስርጭት መጠኑ አሁንም በአንጻራዊነት ሁኔታ ዝቅተኛ ነው።
ጣሊያን ከ12 አመት በላይ ለሆኑት ዜጎቿ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ክትባት ብትሰጥም ባለፈው ሳምንት ውስጥ አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በ16.6 በመቶ ጨምሯል።
ከመስከረም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖርቹጋል የስርጭት መጠን ከ 1000 በላይ ሆኗል። ረቡዕ 2287 ሰዎች በቫይረሱ የታዩዛበት ስፔን የስርጭት መጨመር ካላዩት ጥቂት ሃገሮች አንዷ ሆናለች።