6 ህዳር 2021, 09:10 EAT

የአሜሪካው ድርጅት-ፋይዘር ኮቪድን ለማከም ያበለጸገው ክኒን በጠና የታመሙ አዋቂ ሰዎችን ሆስፒታል የመግባት ወይም የመሞት ዕድላቸውን 89 በመቶ እንደሚቀንስ የተደረገው ሙከራ አመለከተ።
ፓክስሎቪድ የተባለው መድኃኒት ለጽኑ ህመም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የበሽታውን ምልክት ካሳዩ በኋላ ወዲያውኑ ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ የበለጸገ ነው።
ፋይዘር ይህንን ይፋ ያደረገው የዩናይትድ ኪንግደም የመድኃኒት ተቆጣጣሪ መርክ ሻርፕ ኤንድ ዶም (ኤም.ኤስ.ዲ) በተባለ ድርጅት የበለጸገውን ተመሳሳይ መድኃኒት ካጸደቀ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ፋይዘር የመጀመሪያው የሙከራ ውጤት አዎንታዊ በመሆኑ ሙከራዎቹን ቀደም ብሎ ማቆሙን ገልጿል።
ዩናይትድ ኪንግደም በፋይዘር የተመረተውንና እስካሁን ያልተረጋገጠውን 250 ሺህ ክኒን እንዲሁም 480 ሺህ በኤምኤስዲ የተመረተውን ሞልኑፒራቪር ክኒን አዝዛለች።
- በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 5 ሚሊዮንን መሻገሩ ተሰማ
- እያንዳንዳችን የምናመነጨውን በካይ ጋዞችን እንዴት መቀነስ እንችላለን?
- ለ60 ህጻናት የልብ ህክምና 6 ሚሊዮን ብር ያሰባሰበች የበጎ ፍቃድ አምባሳደር
የዩናይትድ ኪንግደም [ዩኬ] የጤና እና የማኅበራዊ እንክብካቤ ኃላፊ ሳጂድ ጃቪድ የሙከራ ውጤቱን “አስደናቂ” ያሉት ሲሆን የዩኬ መድኃኒት ተቆጣጣሪ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑንና ውጤታማነቱን እንደሚገመግም ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም “መድኃኒቱ አገልግሎት ላይ እንዲውል ከተፈቀደ ቫይረሱን ለመከላከል ለምናደርገው ትግል ከክትባቱና ከሌሎች ሕክምናዎች ጎን ለጎን ሌላኛው መሣሪያ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ፕሮቴስ ኢንሂቢተር የተባለው የፋይዘር መድኃኒት ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ለመባዛት የሚጠቅመውን ኢንዛይም እንዲቆም ለማድረግ የተሠራ ነው።
መድኃኒቱ በዝቅተኛ መጠን ሪቶናቪር ከተባለ ከሌላ ፀረ ቫይረስ ክኒን ጋር ጎን ለጎን ከተወሰደ በሰውነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ ይቆያል።
መድኃኒቱ ሦስት ክኒኖች በቀን ሁለት ጊዜ ለአምስት ቀናት ይወሰዳል።
አሁንም በሙከራ ላይ ያለው ይህ ጥምር ሕክምና በቫይረሱ ዘረ መል ኮድ ውስጥ ስህተት እንደተገኘበት ካስታወቀው ከመርክ ክኒን ለየት ባለ መልኩ እንደሚሰራም ተነግሯል።
ፋይዘር የመጀመሪያውን የክኒኑን የሙከራ ውጤት ለድንገተኛ ጊዜ እንዲውል ለአሜሪካ መድኃኒት ተቆጣጣሪ (ኤፍዲኤ) ለማስገባት ማቀዱን ገልጿል። ሙሉ የሆነው የሙከራው መረጃ ግን በሁለቱም ድርጅቶች እስካሁን አልታተመም።
እንደ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከሆነ አሜሪካ በሚሊየን የሚቆጠር መጠን ያላቸው እንክብሎችን ለራሷ ይዛለች።
የድርጅቱ ኃላፊ እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አልበርት ቦርላ ክኒኑ የህሙማንን ሕይወት ለመታደግ፣ የኮቪድ-19 ህመም እንዳይባባስ ለማድረግ እንዲሁም ከአስር ታማሚዎች ዘጠኙ በህመሙ ሳቢያ ሆስፒታል እንዳይገቡ እንደሚያስችል ተናግረዋል።