November 9, 2021 – Konjit Sitotaw
❝መቼም አንረሳችሁም❞
ያ አስፈሪ የሞት ጽልመት የማይፋቅ ጠባሳ ……………………………

ያ አስፈሪ የሞት ጽልመት የማይፋቅ ጠባሳውን ጥሎ ካለፈ ከወራት በኋላ የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ማይካድራ ለሌላ ሥራ አቅንቶ ነበር፡፡ ለሕልውና ዘመቻው በአንድ ተሰባስበው ለሠራዊቱ ስንቅ የሚያዘጋጁ የማይካድራ እናቶችን እያናገርን ነው፡፡ ከተሰባሰቡት እናቶች መካከል ዓይኗ እያየ ሕጻን ልጇን እንዳቀፈች ባሏ በግፍ የተገደለባት ሴት እንዳለች ሰማን፡፡ ይህችን ሐዘን ውስጧን የሰበራትን እና የትዳር አጋሯን ግፈኞች በግፍ የነጠቋትን ሴት ልናናግራት ፈልገን ወዳለችበት ሄድን፡፡ ፈቃደኝነቷን አረጋግጠን ለቀረጻ ስንዘጋጅ ከሦስት ዓመት እድሜ ያልበለጣት ልጇ ከአቻዎቿ ጋር ከምትጫዎትበት ቦታ እየተርበተበተች ወደ እናቷ መጥታ “እናቴ ሊያርዱሽ ነው እናቴ ሊያርዱሽ ነው” እያለች ስታለቅስ አስተዋልን፡፡
አዎ! ያንን አስከፊ የጨለማ ሌሊት ኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ የአማራ ሕዝብ ፈጽሞ አይረሱትም፡፡ ሕጻናት አስፈሪው የሞት ጽልመት ከለጋ አዕምሯቸው አልተፋቀም፡፡ ታላላቆቹ የልብ ስብራታቸው ጠሊቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አጥብቃ የምትጠላውን እና የምትጸየፈውን የዘር ጭፍጨፋ በማይካድራ ተፈጽሞ ተመለከተች፡፡
በከተማዋ መካከል ያለ አንድ ቤተ ክርስቲያን ያንን የጅምላ ጭፍጨፋ በሰፊ እድሞ ስር የቀብር ቦታ ሰጥቶ አስተናገደ፡፡ አስፈሪ ከሆነው የሞት ድባብ ፈጽማ ያልተፈዎሰችው ማይካድራ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አካባቢ ድባቡ ግዝፎ ያስፈራል፡፡ ጥላቻ የበላቸው እና ግፈኞች ያረዷቸው ንጹሐን አጽም ያረፈበት መሬት ምሬቱን በዝምታ የሚገልጽ ይመስላል፡፡ የሟቾች አስከሬን የተሸኘባቸው የገመድ አልጋዎች ከወደቁበት አልተነሱም፡፡ ስለእነዚያ ግፉዓን ቀሪዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚሉት ቢያጡ “መቼም አንረሳችሁም” ሲሉ ቁጭታቸውን በአንድ ጣውላ ላይ ጽፈው በመቃብራቸው መካከል ተክለው ተመልሰዋል፡፡
በማንነታቸው ተለይተው እና አማራ በመሆናቸው ብቻ ተመርጠው ሕይዎትን በገፉበት ቀየ በአንድ ሌሊት ብቻ በርካታ ዜጎች በግፍ እና በገፍ ታረዱ፡፡
ሽንፈታቸውን በጸጋ መቀበል የተሳናቸው ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ገዳዮች የፈሪ ቁጭታቸውን በንጹሐን ላይ ተወጡ፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት ጥላቻቸውን ለማወራረድ እና ቂማቸውን ለመበቀል በማይካድራ የሚኖሩ ንጹሐንን ጨፈጨፉ፡፡
ዓለም ስለማይካድራው የዘር ጭፍጨፋ በውድቅት ሌሊት ሰማ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ስለድርጊቱ ማቅ ለበሱ፡፡ ይህ ግን ግፈኞቹን ለማሳደድ እልህ እና ጉልበት ሆነ እንጂ ከአሸናፊነት እርምጃው የገታው ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግፈኞቹን ከገቡበት ገብቶ ለማሳደድ ቀን ከሌሊት ዘብ ቆሟል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል እና የአማራ ሚሊሻ ቅልቦቹን የሳምሪ ገዳይ ቡድን አባላት እያነፈነፉ ይከተላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሰማይ በታች ከፍ ብሎ ገዳዮች ሊደርሱበት ይችላሉ የተባሉ ቦታዎችን ኹሉ እሳት እየተፋ ዶግ አመድ ያደርጋቸዋል፡፡
የወገን ጦር ጥምረት የሞቱትን ሕይዎት መመለስ ባይችል እንኳን ግፈኞች የእጃቸውን እንዲያገኙ የሚቻላቸውን ኹሉ ያለስስት እና ርህራሄ እያደረገ ነው፡፡
ያ በማይካድራ ከተማ የተፈጸመ አስፈሪ የሞት ድባብ ዛሬ አንደኛ ዓመቱን አስቆጠረ፡፡ ገዳዮቹ እንደገደሏቸው በግፍ ባይሞቱም እየተንጠባጠቡም ቢሆን በየጊዜው የእጃቸውን አግኝተዋል፡፡ ቀሪዎቹም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ከእውነት እና ከፍትሕ አያመልጡም፡፡ “በግፍ የበለጸገ በግፍ ይደኽያል” እንዳለ መጽሐፍ ግፈኞች የክፉ ሥራቸውን ልክ ያገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ በኋላም መራር የሚባሉ የዘር ጭፍጨፋዎችን ባሳለፍነው ዓመት ውስጥ አይታለች፡፡ ግን ሊነጋ ሲል እንዲጨልም እውነት ነው፡፡ ከጨለማው በኋላ የኢትዮጵያ ቀን በማይካድራ ሳይቀር ይበራል፡፡
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!
