ጂቡቲ በጎረቤቶቿ ላይ ለሚፈጸም ጣልቃ ገብነት ግዛቷ መጠቀሚያ እንደማይሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ አገራቸው “በጎረቤት አገር ላይ ለሚፈጸም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መጠቀሚያ ሆና እንደማታገለግል” ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በጂቡቲ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ከፍተኛ ወታደራዊ ጄነራል ዊሊያም ዛና፤ በኢትዮጵያ ቀውስ የሚከሰት ከሆነ የአሜሪካ ወታደሮች “ከእዚህ ምላሽ ይሰጣሉ” በማለት ለቢቢሲ ከተናገሩ በኋላ ነው።
“አንዳንዶች የጂቡቲ ግዛት በጎረቤት አገራት ላይ ለሚፈጸም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል” በማለት የጄነራሉን ንግግር ተከትሎ የተፈጠረውን ስሜት የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ ግን እንደማይሆን ገልጸዋል።
“ከጎረቤቶቹ ጋር ትስስር ያለው የጂቡቲ መንግሥት ይህ እንዲሆን አይፈቅድም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።
https://twitter.com/ymahmoudali/photo
ለቀይ ባሕር ስልታዊ መተላለፊያ በሆነችው ጂቡቲ ውስጥ የጦር ሰፈርና ወታደሮች ካሏቸው አገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀውስ የሚፈጠር ከሆነ ወታደሮቿ ምላሽ እንደሚሰጡ ጄነራሉ ገልጸው ነበር።
ጦርነቱ በተፋፋመበት በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በአማጺያኑ እጅ የምትወድቅ ከሆነ አሜሪካውያንን ለማስወጣት ካምፕ ለሞኒዬር ከሚባለው የጦር ሰፈሯ ወታደሮቿ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
በጂቡቲ የአሜሪካ ጦር አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ዊሊያም ዛና ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለቀጠናው ስጋት ይሆናል።
በአፍሪካ ግዙፉን የአሜሪካ የጦር ሰፈር የሚመሩት ጄነራል ዊሊያም፤ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ግጭት በቀጠናው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራዋል ብለዋል።
ጄነራሉ አያይዘውም “አዲስ አበባ በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር ብትወድቅ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ይከሰታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጄነራል ዊሊያም ጨምረውም በጂቡቲ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ዋነኛ ዓላማው በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ በቀውስ ወቅት ምላሽ መስጠት መሆኑን ጠቅሰው፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞችንና አሜሪካውያንን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ዕቅድ ማውጣታቸውንና ዝግጅት ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ አብዛኛው ወደ አገሯ የሚገባውንና ከአገሯ የሚወጣውን ምርት ለማጓጓዝ የጂቡቲ ወደብን የምትጠቀም ሲሆን በሁለቱ አገራት በኩል ጠንካራ ወዳጅነት አለ።