20 ህዳር 2021, 08:04 EAT

እራሷን ኢንሱሉን የምትወጋ ወጣት
የምስሉ መግለጫ,አይነት አንድ የስኳር ህመም በልጅነት ወይም በጎልማሳነት የሚያጋጥም ሲሆን ይህም በዘር ወይም በተለያዩ በሽታዎች ሰበብ ሊከሰት ይችላል

በተለምዶ የስኳር ህመም እያልን የምንጠራው ዳያቢቲስ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሞት ይዳርጋል።

የስኳር ህመም ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ የሚችል በሽታ ነው።

በሽታው የሚመነጨው በሰውነታችን የደም ቧንቧ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ሳይችል ሲቀር ነው። ይህም ለልብ በሽታ፣ ለደም ዝውውር መስተጓጎል፣ ዕይታ ለማጣት፣ ለኩላሊት ህመም እንዲሁም ለእግር መቆረጥ ሊያጋልጥ ይችላል።

የስኳር ህመም አሁንም እየተስፋፋ ያለ በሽታ ነው። ከዓለም ሕዝብ 422 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ይህ ህመም እንዳለባቸው ይገመታል። ይህ አሃዝ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በአራት እጥፍ ከፍ ያለ ነው ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።

ምንም እንኳ በሽታው ገዳይ ቢሆንም ህመሙ ካለባቸው ግማሽ ያክሉ ስለበሽታው ያላቸው ዕውቀት ውሱን ነው።

ነገር ግን ይህን በሽታ የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር መከላከል ይቻላል። እነሆ መላው፡

በሽታውን የሚያስከትለው ምንድነው?

ስንመገብ ሰውነታችን የሚቀለበውን ካርቦሃይድሬት የተሰኘ ንጥረ ነገርን ወደ ስኳር ወይም ግሉኮስ ይቀይረዋል። ይህንንም ከጣፊያችን የሚመነጨው ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን የሰውነታችን ህዋሳት ስኳሩን ወደ ኃይልነት እንዲቀይሩ ያደርጋሉ

የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ኢንሱሊን ሳያመነጭ ሲቀር አሊያም በአግባቡ መሥራት ሳይችል ሲቀር ነው። ይህ ክስተት በደማችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ከፍ ያደርገዋል።

የስኳር አንኳሮች እና ስኳር በማንኪያ
የምስሉ መግለጫ,የተጣራ ስኳር በደማችን ውስጥ የሚገኝን የጉሉኮስ መጠን ይጨምረዋል

የስኳር ህመም ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?

ብዙ የስኳር በሽታ ዓይነቶች አሉ።

የመጀመሪያውን ዓይነት የሚከሰተው ጣፊያ ኢንሱሊን ማመንጨት ሲያቆምና ግሉኮስ በደም ቧንቧችን ውስጥ ሲጠራቀም ነው።

ሳይንቲስቶች ይህ የሚሆነው ለምን እንደሆነ እስካሁን ባይደርሱበትም ምክንያቱ ከዘር የሚመጣ አሊያም ደግሞ ጣፊያን በሚያጠቃ ሕመም ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። ህመሙ ካለባቸው 10 በመቶው በዚህ ምድብ ይገኛሉ።

ሁለተኛው ዓይነት የሚከሰተው ጣፊያ በቂ ኢንሱሊን ማምረት ሳይችል ሲቀር አሊያም በአግባቡ መሥራት ሲያቆም ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚከሰተው በመካከለኛ ዕድሜ ባሉንና ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ ነው። ነገር ግን የሰውነት ክብደታቸው ከፍ ያለ ወጣቶች እንዲሁም በደቡብ እስያ የሚኖሩ ሰዎች ለዚህ ተጋጭነታቸው የሰፋ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ነብሰ ጡር ሴቶች ለራሳቸውና ማህፀናቸው ውስጥ ላለ ጽንስ በቂ ኢንሱሊን ማምረት ሳይችሉ ሲቀሩ ‘ጄስቴሽናል’ የተሰኘ የስኳር ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል።

የተለያዩ ጥናቶች ከ6 እስከ 16 በመቶ ነብሰ ጡር ሴቶች የዚህ የስኳር ህመም ዓይነት ተጠቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመላክታሉ።

ነብሰ ጡር እናቶች የአመጋገብ ዘይቤያቸውን፣ የሰውነት እንቅስቃሴያቸውን እንዲሁም የኢንሱሊን መጠናቸውን ካልተቆጣጠሩ ለሁለተኛው የበሽታው ዓይነት ሊጋለጡ ይችላሉ።

ሌላኛው የስኳር ህመም ዓይነት ‘ፕሪ-ዳያቢቲስ’ ይባላል። ይህ የሚከሰተው በደማችን ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን ከፍ ያለ ሲሆን ነው።

የጣፊያ ሥዕል
የምስሉ መግለጫ,በጣፊያችን የሚመረተው ኢንሱሊን ሰውነታችንን የጉሉኮስ መጠንን ለመቆጣጠር ያስችለዋል

የስኳር ህመም ምልክቶች

የተለመዱ የስኳር ህመም ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡

እንደ ብሪታኒያ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ከሆነ የመጀመሪያው ዓይነት የስኳር ህመም ምልክቶች ከልጅነት ጀምሮ የሚከሰቱና እያደግን ስንመጣ የሚጠነክሩ ናቸው።

በሁለተኛው ዓይነት የሚጠቁት ደግሞ ዕድሜያቸው 40 እና ከዚያ በላይ የሆኑ [በደቡብ እስያ 25] እንዲሁም የቤተሰብ አባል በበሽታው የተጠቃባቸው፣ ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት ያላቸውና ደቡብ እስያዊ፣ ቻይናዊ፣ አፍሮ ካሬቢያንና ጥቁር አፍሪካዊያን ናቸው።

የስኳር ህመምን መከላከል ይቻላል?

የስኳር ህመም በዘር ግንድና ነምንኖርበት አካባቢ ላይ ጥገኛ ቢሆንም ጤናማ አመጋገብ በመከተልና ንቁ በመሆን የሰውነታችንን የግሉኮስ መጠን መቆጣጠር እንችላለን።

የታሸጉ ስኳር ያለባቸው መጠጦችና ምግቦችን ማስወገድ እንዲሁም በነጭ ዳቦና ፓስታ ምትክ የገብስ ዳቦ መመገብ እንደ መጀመሪያ ደረጃ መከላከያ ይቆጠራል።

ተጣርተው የሚመረቱ ጥራጥሬዎችና ስኳር ውስጣቸው ያለው ንጥረ ነገር አነስተኛ ነው። ይህ የሚሆነው በቫይታሚን የበለፀገው ክፍላቸው እንዲሁም ፋይበር [አሰር] በምርት ሂደት ስለሚወገድ ነው።

በተለምዶ ፉርኖ ዱቄት የምንለው፣ ነጭ ዳቦ፣ ነጭ ሩዝ፣ ነጭ ፓስታ፣ ጣፋጭ ምግቦች [ኬክና መሰሎቹ]፣ ስኳር ያለባቸው መጠጦችና ስኳር የተጨመረባቸው የቁርስ ጥራጣሬዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ፍራፍሬና ያልተጣራ ጥራጥሬ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ከሚመደቡ መካከል ናቸው። ጤናማ ዘይት፣ ለውዝ፣ ኦሜጋ 3 ያላቸው እንደ ሳርዲን፣ ሳልመንና ማኬሬል ያሉ ዓሳዎችም ይመከራሉ።

ስንመገብ ሰዓታችንን ጠብቀን ቢሆንና ከልክ በላይ ባንመገብ መልካም ነው ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።

የሰወነት እንቅስቃሴ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቀነስ ይረዳል። የብሪታኒያ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት በሳምንት ቢያንስ ለ2.5 ሰዓታት እንደ ፈጣን እርምጃና ደረጃ መውጣት ያሉ እንቅስቃሴዎች ማድረግን ይመክራል።

ጤናማ የሰውነት ክብደት በሰውነት ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ይረዳል። ክብደትዎን ለመቀነስ ካሰቡ ቀስ በቀስ ቢያደርጉት ይመከራል። ለምሳሌ በሳምንት ከ0.5 እስከ 1 ኪሎግራም።

ፍራፍሬዎች፣ ጥራጥሬዎች እና ጤናማ የዘይት ውጤቶች
የምስሉ መግለጫ,በፋብሪካ የጠጣራ ስኳርንና ዱቄቶችን በፍራፍሬና ባልተቀናበሩ ጥራጥሬዎች መተካት በደማችን ውስጥ ያለን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ይረዳል

የስኳር ህመም ምን ያስከትላል?

በደም ቧንቧ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መጨመር የደም ሥርን ሊጎዳው ይችላል።

ደም በሰውነታችን በአግባቡ መንሸራሸር ካልቻለ ወደ አስፈላጊው የሰውነታችን ክፍል ላይደርስ ይችላል። ይህ ደግሞ የነርቭ ችግር ያስከትላል። አልፎም የዕይታ እክልና የእግር በሽታ ያመጣል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳያቢቲስ በዓለማችን ትልቁ የዕይታ ማጣት ምክንያት ነው ይላል። በተመጨማሪም ለልብ በሽታ፣ ለደም ግፊትና ለእግር መቆረጥ ያጋልጣል።

በፈረንጆቹ 2016 ቢያንስ 1.6 ሚሊዮን ሰዎች በስኳር ህመም ምክንያት እንደሞቱ ይገመታል።

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 1980 በዓለማችን የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 108 ሚሊዮን ነበር፤ አሁን ግን 422 ሚሊዮን ደርሷል ይላል።

በ1980 አምስት በመቶ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የስኳር ህመም ነበረባቸው። ይህ አሃዝ አሁን ወደ 8.5 በመቶ ከፍ ብሏል።

ዓለም አቀፉ የዳያቢቲስ ፌዴሬሽን እንደሚገምተው የስኳር ህመም ካለባቸው ሰዎች 80 በመቶ ያክሉ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ውስጥ ነው የሚኖሩት።

አደጉ በሚባሉ አገራት የስኳር ህመም የሚያጠቃው ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ ርካሽና የታሸጉ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎችን ነው።