ከ 6 ሰአት በፊት

ምርመራ እየተደረገለት ያለ ሰው

በደቡባዊ አፍሪካ በሚገኙ አገራት የተገኘ አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ አዲስ ስጋት መቀስቀሱ ተገለጸ።

ይህን ተከትሎም ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከደቡብዊ አፍሪካ አገራት ወደ እንግሊዝ የሚገቡ ተጓዦች ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ የሚያስገድድ ሕግ አውጥታለች።

ይህም የሆነው በደቡባዊ የአፍሪካ አገራት በዓይነቱ የተለየ፣ በመዛመት ፍጥነቱ የከፋ ነው የተባለ አዲስ የኮቪድ ዝርያ መገኘቱን ተከትሎ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚኒስትር ሳጂድ ጃቪድ ከአርብ ጀምሮ ስድስት የደቡባዊ አፍሪካ አገራት ለጉዞ አሳሳቢ በተባለው ምድብ ዝርዝር ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።

አንድ ባለሙያ ይህን አዲስ ዝርያ B.1.1.529 በሚል የጠሩት ሲሆን እስከዛሬ ከታዩ ዝርያዎች ሁሉ የከፋው ነው ተብሏል።

እስከ አሁን በዩኬ አንድም በዚህ ዝርያ የተያዘ ታማሚ ሪፖርት አልተደረገም።

በዚህ ዝርያ ተይዘው የተገኙ 59 ሰዎች ብቻ ሲሆኑ እነሱም በደቡብ አፍሪካ፣ በሆንግ ኮንግና በቦትስዋና ውስጥ ነው ሪፖርት የተደረጉት።

ይህን ተከትሎም ከደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ቦትስዋና፣ ሌሴቶ እና ኢስዋቲኒ ማንኛውም በረራዎች ወደ እንግሊዝ ምድር እንዳይደረጉ ታግደዋል።

የዩኬ ጤና ሚኒስትር እንደተናገሩት ይህ አዲስ ዝርያ በርካታ ሳይንቲስቶችን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።

ስለ ዝርያው ለጊዜው ብዙ እንደማይታወቅና ገና እየተጠና እንደሆነም ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ይህ ዝርያ ራሱን የሚያባዛበት መንገድ አስደንጋጭ እንደሆነና ዴልታ ከተባለው ዝርያ እጥፍ ራሱን እንደሚያባዛ ጠቁመዋል።

ይህም ማለት ከሰዎች ወደ ሰዎች የሚዛመትበት ፍጥነት ከእስከዛሬው የበለጠ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።

እስከ አሁን የተሰሩ ክትባቶችም ለዚህ ዝርያ መከላከያነት ይሆናሉ አይሆኑም የሚለው ገና የሚጠና ይሆናል።

ይህ ዝርያ በጥናት ወረቀቶች ላይ እንደተገለጸው ከእስከዛሬዎቹ የኮቪድ ዝርያዎች ሁሉ የከፋ ይባል እንጂ ምን ያህል ገዳይ ነው፣ ተዛማችነቱ በምን ፍጥነት ነው፣ ክትባቶች ያቆሙታል ወይ የሚለው ገና ዝርዝር ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው ተብሏል።