3 ታህሳስ 2021, 08:01 EAT

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን በአሜሪካ መታየቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጠበቅ ያሉ የጉዞ መመሪያዎችን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ስለ መመሪያው ሲያወሩ ”ዕቅዳችን ሙሉ በሙሉ መዝጋት አይደለም። ከክትባት ጋር የተያያዙ ቁጥጥሮችን ለመጨመርም አይደለም” ብለዋል።
በካሊፎርኒያ፣ ኮሎራዶ፣ ሚኒሶታ፣ ኒው ዮርክ እና ሃዋይ ኦሚክሮን የተሰኘው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዓይነት መታየቱን የጤና ባለሥልጣናት ያስታወቁ ሲሆን ሰዎቹም ምንም አይነት የጉዞ ታሪክ የላቸውም።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቀለል ያለ ምልክት ብቻ እንዳሳዩ የግዛቶቹ የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
እስካሁን ድረስም በጊዜ ብዛት እራሱን የቀየረው ቫይረስ ትኩረቱ በብዛት መሰራጨት ላይ ነው ወይስ ክትባቶችን መቋቋም የሚለው አልታወቀም።
- በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት መቀነሱ ተገለጸ
- በደቡብ አፍሪካ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨመረ
- ጀርመን ያልተከተቡ ዜጎቿ በሱቆች እና መጠጥ ቤቶች መገኘት አይችሉም አለች
በደቡብ አፍሪካ ባለፉት ቀናት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 8 ሺህ 500 የተጠጋ ሲሆን፤ ከዛ ቀደም ባለው ቀን ተመዝግቦ የነበረው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ሺህ 300 የሚጠጋ ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት ቢያንስ በ24 አገራት አዲሱ ኦሚክሮን የኮሮናቫይረስ ዝርያ መገኘቱን አስታውቋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ በቅርቡ ይህ ቫይረስ የተገኘባቸው አገራት ናቸው። ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን እና ቤልጂየም እንዲሁ ኦሚክሮን ከተገኘባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ይህን ቫይረስ ቀድማ ሪፖርት ያደረገችው ደቡብ አፍሪካ ነበረች። የአገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት ካለፈው የፈረንጆቹ ወር ወዲህ በምርመራ ካረጋገጣቸው የኮሮናቫይረስ ኬዞች መካከል ኦሚክሮን የ70 በመቶ ድርሻ እንዳላው አስታውቋል።
በዚህ ቫይረስ ተይዘው ወደ ሆስፒታል ከመጡት መካከል አብዛኛዎቹ የኮቪድ-19 ክትባት ያልወሰዱ መሆናቸውንም ተቋሙ አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኦሚክሮን የመዛመት ዕድሉ ከፍተኛ ነው በማለት “አሳሳቢ ዝርያ” ሲል ፈርጆታል።
በአዲሱ መመሪያ መሠረት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስብ ሰው ክትባቱን ወሰደም አልወሰደም ከጉዞው 24 ሰዓት በፊት ተመርምሮ ቫይረሱ እንደሌለበት ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት።
እስከመጪው መጋቢት ወር ድረስም አውሮፕላኖች ውስጥ፣ ባቡር ውስጥ እንዲሁም የሕዝብ ማመመላለሻዎች ውስጥ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ አለባቸው።
የአሜሪካ መንግሥት ወጪውን መሸፈን የሚችል ኢንሹራንስ ያላቸው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነጻ ምርመራ እንዲያገኙ ለማድረግም ዕቅድ አለው።