December 13, 2021 

ይህ የምታዩት ካርታ ከሞላ ጎደል አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። በአረንጓዴ የተቀቡ አካባቢዎች፣ ችግር፣ ጦርነት ፣ ውድመት የነበረባችው አሁን ግን በአንጻራዊነት መረጋጋትና ሰላም የሰፈነባቸው አካባቢዎች ናቸው። ብርቱካማ ቦታዎች ከሕወሃት ጋር ዉጊያ እየተደረገባቸው ያሉ፣ ሕወሃቶች አሁንም ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው። በቢጫ የተቀቡት ኦነግ አሁንም የሚንቀሳቀስባቸው ፣ ከኦነግ ያልጠሩ አካባቢዎች ናቸው። ቀያማ አካባቢዎች በሕወሃት ስር ያሉ አካባቢዎች ናቸው።እንግዲህ ላለፊት አራት አመታት በኢትዮጵያ መጥቷል ተብሎ የተነገረው መደመርና ብልጽግና ይሄን ነው የሚመስለው። የብልጽግና መንግስት አገሪቷን እንዲህ አይነት ትርምስ ውስጥ ነው የከተታት። አሁን ሕዝ በሁሉም አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ያለው፣ ብልጽግናዎች አገሪቷን ካስገቡባር አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ነው።

ሌላው አረንጓዴ የተቀቡ ቦታዎች መብዛታቸው ሕዝባዊ ትግሉ ምን ያህል ውጤት እንዳመጣም አመላካች ነው። ምንም እንኳን በነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ ውድመት የደረሰ ቢሆንም፣ ቢያንስ የወገን ጦር አሸባሪዎችን ማጽዳት ችሏል። ሕልማቸውን አጨናግፎባቸዋል። በቅርቡም ብርቱካማ የሆኑ ወደ አረንጓዴነት ይቀየራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በቀይ የተቀቡ አካባቢዎች

===========

ትግራይ፣ ጠለምትና ራያ በወያኔ ስር ናቸው። ጠለምትን መልሶ የመያዝ አቅም አለ። ግን ለምን የማጥቃት ዘመቻ እንደማይደረግ ለብዙዎች ግልጽ አይደለም። ራያም የወገን ጦር በቀላሉ የማስለቀቅ አቅም አለው። የአብይ መንግስት “ራያ የትግራይ ናት” በሚል የወገን ጦር ወደፊት እንዳይገሰግስ እንቅፋት ካልሆነ በቀር ራያን ማስለቀቅ አስቸጋሪ አይሆንም።የትግራይ ነገር የተለየ ስትራቴጂ ያስፈልገዋል። የወገን ጦር ትግራይን መልሶ መያዝ ይችላል፣ አለበትም። ነገር ግን አንደኛ የአብይ መንግስት ያንን የመወሰን ፍላጎት አለው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው። ከህወሃቶች ጋር የመደራደር ፍላጎት እንዳላ እየተሰማ ነው። ሁለተኛ የወገን ጦር ትግራይን ቢይዝም ሰላምን ማስፈን ማስተዳደርም መቻል አለበት፡፡ ያለፈው ጊዜ የሆነው እንዳይደገም፣ ወያኔን የመደምሰስ ስራ የትግራይን ሕዝብ ባቀፈ መልኩ መሆን አለበት። ስለዚህ ወደ ትግራይ ጦርነት ከመከፈቱ በፊት ሕዝቡን ከሕወሃት የመነጠል የፖለቲካ ሰራ መሰራት አለበት። የትግራይ ተወላጆችን በአዲስ አበባ ሌሎች ቦታዎች በጅምላ በማንነት ማሰር ስህተት ነው የምንለው አንዱ ከዚህ የተነሳ ነው።

ብርቱካማ አካባቢዎች

==========

ብርቱካማ አካባቢዎች ዉጊያ ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በስሜን ጎንደር ዞን የአደርቃይ ወረዳ፣ ግማሹ የዋገምራና የስሜን ወሎ ወረዳዎች የዉጊያ ቀጠናዎች ናቸው። በአደርቃይ፣ ከላይ እንዳልኩት ጠለምትን ጨምሮ የወገን ጦር አካባቢዉን ሙሉ ለሙሉ የማጽዳት አቅም አለው። ነገር ግን ትእዛዝ ስላልተሰጠ በዚያ በዛሪማ መስመርም ያለ እጅግ በጣም ከፍተኛ ጦር ቁጭ ብሎ እየጠበቀ ነው።

በሰቆጣ፣ በኮረምና በቆቦ መስመሮች ወደ መቀሌ የሚወስዱ መንገዶች ስለተዘጉ እጅግ በጣም በርካታ የሕወሃት ጦር በዋገምራና በስሜን ወሎ ይገኛል። ተቆርጦ። በአሁኑ ጊዜ ሰብሮ ወደ ትግራይ ለማምለጥ በጋሸና፣ ላሊበላ በኩል መንገድ ለማስከፈት ወያኔዎች እየተዋጉ ነው።

አረንጓዴ አካባቢዎች

==========

አረንጓዴ አካባቢዎች ዉጊያና አለመረጋጋት የነበረባቸው፣ ግን አሁን በአንጻራዊነት የተረጋጉ ከአሸባሪ ቡድኖች የጸዱ አካባቢዎች ናቸው።ከአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ወያኔ ብዙ ጊዜ ጦርነት ከፍታ አልቻለችም። በምእራብ ጎንደር በሽንፋ በኩል ሳምሪ የተሰኘው የወያኔ ቡድን በሱዳኖች እየታገዘ ብዙ ሙከራ አድርጓል። በሰሜን ጎንደር ዳባትና ደባርቅ ወረዳዎች ወያኔ ገብታ ነበር። በደቡብ ጎንደር ዞን በምእራብ በኩል እስከ ደብረ ታቦር ጫፍ ደርሳ ነበር። በዋገመራ እንደ ደሃና፣ በሰሜን ወሎ እንደ ዳዎንት፣ መቄት ያሉ ወረዳዎች ነጻ ወጥተዋል። በስሜን ሸዋ ይፋትና መንዝ ያሉ ወረዳዎች እንዲሁም ሙሉ ደቡብ ወሎ ወያኔ ገብታ ነበር። ሆኖም እነዚህ ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ ነጻ ወጥተዋል።

በአፋር ክልል በዞን 1፣ ዞን 2፣ ዞን 4 እና ዞን 5 አንዳንድ ወረዳዎች ወያኔ ገብታ ጥቃቶች ፈጽማለች። በተለይም ሚሌን ለመያዝ በተለያዩ ጊዚያት በተለያዩ አቅጣጫዎች ያደረገችው ዉጊያ አልተሳካላትም።፡በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ከፍተኛ እልቂትና ጄኖሳይድ የነበረበት አካባቢ ነበር። በዚያ የጉሙዝ አሸባሪዎች፣ ኦነጎች በጥምረት በመሆን ብዙ ጥፋት፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሲፈጽሙ ነበር። አሁንም የአማራ ልዩ ኃይል ወደዚያ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ መተከል በአንጻራዊነት መረጋጋት ያለባት አካባቢ ሆናለች።

ቢጫማ አካባቢዎች

=========

እነዚህ አካባቢዎች የኦነግ ታጣቂ ኃይል የሚንቀሳቀስባቸው፣ ከኦነግ ያልጸዱ አካባቢዎች ናቸው።በቅርቡ የወገን ጦር፣ ከሕወሃትና ከኦነግ ጥምረት፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተባለውን ነጻ ማውጣቱን የመንግስት ሜዲያዎች ዘግበዋል። እርግጥ ነው በኦሮሞ ብሄረሰብ ገብተው ከነበሩ የሕወሃት ታጣቂዎች ዞኑ ጸድቷል። ሆኖም ግን አሁንም የኦነግ ታጣቂዎች በዞኑ አሉ። ታክቲካል ማፈግፈግ በማድረግ፣ መሳሪያቸውን ደብቀው፣ ሰላማዊውን ማህበረሰብ በመቀላቀል ሌላ አመች ጊዜ እየጠበቁ ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የሚባለው አሁንም በተለይም ለሰሜን ሽዋ ሕዝብ ትግል የስጋት ቀጠና የሆነ ነው። ከአሸባሪዎች ነጻ ወጥቷል ማለት አይቻልም።

የቤኔሻንጉል ክልል የከማሺ ዞን፣ የኦሮሞ ክልል የምስራቅ፣ የምእራብ፣ የቄሌምን የሆሮጉድሩ ወለጋ ዞኖች፣ የምእራብ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ አንዳንድ ሰሜናዊ ምእራብ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በጉጂ ዞን አሁንም ኦነግ እየተንቀሳቀሰባቸው ያሉ አካባቤዎች ናቸው። የብልጽግና መንግስት ይኸው ላለፊት 2 አመታት ኦነጎችን ሽፍቶች ናቸው፣ ተደምሠዋል እያለ ህዝቡን እየዋሸ የነበረ፣ አሁን እየዋሸ ነው። ሆኖም ግን በብዙ ቦታዎች ነገሮች ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው።ከአምሳ ጊዜ በላይ ዙር ሰለጠነ የተባለው የኦሮሞ ክልል ልዩ ኃይል ከአመራር ብቃት ይሁን፣ ወይንም በውስጡ ለኦነግ የሚሰሩ መኮንኖች በመኖራቸው፣ ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። በዚያ የመከላከያ ስምሪት ተድርጎ ውጤት አልመጣም።እነዚህን አካባቢዎች ለምን ከኦነግ ማጻዳት አልተቻለም የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ጥያቄ ነው። መንግስት አቅም ስላጣ ነው ? ነው ወይስ ፍላጎት ስለሌለ ነው ???