13 ታህሳስ 2021, 10:15 EAT

ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና ቻይና የኮሪያን ጦርነት በይፋ ለማቆም ‘በመርኅ ደረጃ’ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ሙን ኤ ኢን ተናገሩ።
ይሁንና ጦርነቱን ለማቆም ገና በንግግር ደረጃ እንደሆኑ ሙን ተናግረዋል። ሂደቱ የዘገየውም ሰሜን ኮሪያ ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳቷ ነው።
እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ከ1950 እስከ 1953 የተደረገው የኮሪያ ጦርነት በተኩስ አቁም እንጂ በሰላም ስምምነት አልተጠናቀቅም።
- ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ዳግም በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር መግባቷ ተዘገበ
- አሜሪካ በአማራና በአፋር በህወሓት ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎች አሳስበውኛል አለች
- የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በጦር ኃይሉ ተሹመው የነበሩ አስተዳዳሪዎችን አሰናበቱ
ይህ በመሆኑም ሁለቱ ኮሪያዎች አሁንም ድረስ ጦርነት ላይ እንደሆኑ ነው የሚታሰበው።
ሰሜን ኮሪያ በቻይና ስትደገፍ፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ በአሜሪካ እየተደገፉ አካባቢው ለአስርታት በውጥረት ውስጥ እንዲቆይ አድርጓል።
ሰሜን ኮሪያ የምትፈልገው ምንድነው?
ባለፈው ጥር የኪም ጆንግ ኡን እህትና ሰሜን ኮሪያን ከመጋረጃ ጀርባ ከሚመሩት አንዷ የምትባለው ኪም ዮ ጁንግ አገሯ ሰሜን ኮሪያ ለድርድር ክፍት መሆኗን የሚጠቁም ንግግር አድርጋ ነበር።
ነገር ግን ንግግሩ የሚሳካው አሜሪካ በሰሜን አሜሪካ ላይ የጠላትነት ፖሊሲዋን ያነሳች ጊዜ ብቻ ነው ብላ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ወታደሮች በደቡብ ኮሪያ መኖራቸው ያበሳጫታል። ሰሜን ኮሪያና አሜሪካ በየዓመቱ የጋራ የጦር ልምምድ ያደርጋሉ።
አሜሪካ በበኩሏ ፖሊሲዋን ለመለወጥ ሰሜን ኮሪያ በቅድሚያ አደገኛ የኒውክሊየር መሣሪያ ግንባታ ውጥኗን እርግፍ ማድረግ ይኖርባታል ትላለች።
ፕሬዝዳንት ሙን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመግባባት ብዙ የጣሩ መሪ ሲሆኑ ከወራት በኋካ ግን ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።
ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት ግን ከጎረቤታቸውና ‘ወንድም-እኅት’ ሕዝብ ከሆነው ሰሜን ኮሪያ ጋር ዘላቂ ሰላም ማውረድና ታሪክ ሠርተው ማለፍን ይሻሉ።
የተባለው የሰላም ስምምነት የሚፈረም ከሆነ፣ ፒዮንግያንግ ምናልባት አሜሪካ በጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ያሰፈረቻቸውን 28 ሺህ ወታደሮቿ አካባቢውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቀው እንዲወጡ ልትጠይቅ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።
እአአ 1950 ተቅስቅሶ በነበረው ጦርነት በሰሜን ኮሪያ በኩል ቻይና እና የሶቪየት ሕብረት እንዲሁም በደቡብ ኮሪያ በኩል አሜሪካ ተሰልፋ አምስት ሚሊዮን ሕይወት የቀጠፈ ጦርነት ተካሂዷል።