አጣዬ ከተማ አሁንም ኦነግ ሸኔ ቡና ሲጠማው ጎራ ብሎ ጠጥቶ የሚወጣባት መዝናኛ ስፍራው ነች።

ከከተማዋ ነዋሪዎች 80 በመቶ የሚሆነው ተሰዶ ሌሎች ጎረቤት ከተሞች ይኖራል። በዚህ ወቅት ወጋገን ባንክ ብቻ ነው በከተማዋ ስራ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ያለው። የከተማዋ 20% ህዝብ በኦነግና በወያኔ ከደረሰበት በደል ለማገገም ጥረት ላይ ይገኛል። በከተማዋ ብዙ ቤቶች አሉ ግን ሰው አይኖርባቸውም። አብዛኞቹ ንግድ ቤቶች ዝግ ናቸው።
ሁሉም ማለት ይቻላል የተዘጉት። ከተማዋ ውስጥ የነበሩ ትምህርት ፣ የጤና ተቋማት በህወሃትና በሸኔ ጥምረት ተዘርፈዋል። ሸኔ ወደ ከተማዋ ጎራ ብሎ ቡና ሲጠጣ የጀበና ቡና ለምታፈላውና ለአካባቢው ነዋሪ ” ከሸኔ እና ከህወሃት ማነው የበላይ?” ብሎ ይጠይቃል?ነዋሪው “እኔንጃ” ይላል።
ሸኔ “ሸኔ ነው የሚበልጠው፣ የህወሃት አለቃ ሸኔ ነው” ብሎ ደንፍቶ ይሄዳል።የወያኔ ሲቪል ለባሽ በተራው “ከሸኔና ከህወሃት ማነው?” ብሎ ጠይቆ “እንጃ” ላለው የከተማ ነዋሪ “ስለቀዳማይ እና ካልአይ ወያነ ታሪካዊ አመጣጥ ተርኮ፣ የሸኔ አለቃ መሆኑን ሰብኮ ይሰናበታቸዋል።
ከተማዋ በሁለት ሀይሎች ብትናወጥም የአማራ ልዩ ሀይል፣ መከላከያ፣ ፋኖ . . . ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ ነው። ኦነግ በቅርብ የአጣዬ ተራራ ላይ መሽጎ ይገኛል። የከተማዋ ነዋሪ አሁንም የደህንነት ስሜት አይሰማውም። ” ከሸኔ ይሻለኛል ወያኔ” ይላሉ። ሸኔ ከተማዋን በሙሉ በእሳት አንድዶ አቃጥሎ ጠፋ። አሁን በከተማዋ የእሳት ቅሪት የሆነ አሻራ በሰፊው ይታያል። “ወያኔ ገብቶ ዘርፎ ገድሎ ሄደ እንደ ሸኔ ግን እሳት አለቀቀበትም” ይልሀል የከተማዋ ነዋሪ።
ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ለተፈናቃዮች እርዳታ ለመለገስ ከተለያየ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጣን ጋዜጠኞችን ረቡዕ እለት ወደ አጣዬ ወስዶን ያየሁትንና ከከተማዋ ነዋሪ የሰማሁትን ነው በጥቂቱ የነገርኳችሁ። ከተማዋን ስላናወጣት ጦርነት፣ የሬሳ ክምር እና ሌሎችንም ተያያዥ ጉዳዮች በቅርቡ በሐበሻ ወግ ሳምንታዊ መጽሄት አስነብባችኋለሁ።