ከ 6 ሰአት በፊት

ክትባት

በኦሚክሮን ዝርያ ምክንያት ይከሰታል ብላ ለምትጠብቀው አዲስ የወረርሽኝ ማዕበል ዝግጀት ላይ የምትገኘው እስራኤል፤ አራተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ክትባት በመስጠት ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር ለመሆን ማቀዷን ይፋ አደረገች።

የእስራኤል የወረርሽኝ ባለሙያዎች ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ አዛውንቶች እና ለጤና ሠራተኞች አራተኛ ዙር የኮቪድ-19 ክትባት እንዲሰጥ ምክረ ሐሳባቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፤ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሐሳቡን ተቀብለው ለባለሥልጣናት ዝግጅት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ውሳኔው እስራኤል በኦሚክሮን ዝርያ አማካይነት የተከሰተውን የመጀመሪያው የታወቀ ሞት ማክሰኞ ቀን ከመዘገበች በኋላ የተሰጠ ነው።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር እስካሁን 340 የታወቁ በኦሚክሮን ዝርያ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ይፋ አድርጓል።

ምንም እንኳን አራተኛ ዙር ክትባቱን የአገሪቱ ከፍተኛ የጤና ኃላፊዎች ገና ባያጸድቁትም ሦስተኛ ዙር ክትባታቸውን ከወሰዱ ቢያንስ ሦስት ወራትን ላስቆጠሩ ሰዎች እንዲሰጥ መታሰቡን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ዓለምን እያዳረሰ የሚገኘውን የኦሚክሮን ዝርያን ተከትሎ ከፊታችን ያለውን አዲስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕበል እንድናልፈው የሚያግዝ መልካም ዜና ነው” ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤኔት ዜጎቻቸው በፍጥነት የቀረበውን እድል እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።

የኮቪድ-19 ክትባት ገና ሲጀመር እስራኤል ለዜጎቿ በፍጥነት ክትባቱን ያቀረበች ሲሆን በንጽጽርም በርካታ ዜጎቿ ክትባቱን ወስደው ነበር።

ነገር ግን 9̄.3 ሚሊዮን ከሚሆኑ ዜጎቿ ውስጥ 63 በመቶው ብቻ ናቸው ሁለት ዙር ክትባቱን የወሰዱት። ይህም እስራኤል በተወሰነ መልኩ የወጣቶች አገር በመሆኗ እና አንድ ሦስተኛው ዜጋዋ ከ14 ዓመት በታች ከመሆኑ ጋር ይገናኛል።

ይህንን ክፍተት ለመሙላትም እስራኤል ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ሕጻናት ክትባቱን መውሰድ እንዲችሉ ፈቅዳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔትም ባለፈው ሰኞ እንዳሉት ሁሉም ዕድሜው ለክትባት የደረሰ ልጅ በመጪው ሁለት ሳምንታት ውስጥ ቢከተብ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል።

እስእራኤል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ካናዳን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ እቀባ ጥላለች።

ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በእስራኤል ከ1.36 ሚሊዮን በላይ የተረጋገጡ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ያሉ ሲሆን ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።