22 ታህሳስ 2021

ኦሚክሮንን በማግኘታቸው የተወደሱት የደቡብ አፍሪካ ሳይንቲስቶች አዳዲስ የኮቪድ-19 ዓይነቶች የበሽታ መከላከል ሥርዓታቸው በተዳከመ ሰዎች ውስጥ ከሚከሰተው ለውጥ (ሚውቴሽን) ጋር ሊገናኝ ይችላል የሚለውን “በጣም ምክንያታዊ መላምት” እየመረመሩ ነው። የበሽታ መከላከል ሥርዓት ያልታከመ ኤችአይቪን ጨምሮ በሌሎችም ምክንያቶች ሊዳከም ይችላል።
ተመራማሪዎች ኮቪድ-19 ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ባለባቸውና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ የሚያስችላቸውን መድኃኒት ሳይወስዱ በቀሩ ታማሚዎች ላይ ለብዙ ወራት ሊቆይ እንደሚችል ተገንዝበዋል።
“በተለምዶ የበሽታ ተከላካይ ሥርዓታችሁ ሙሉ በሙሉ የሚሰራ ከሆነ ቫይረሱን በፍጥነት ያስወግዳል” ያሉት በኬፕ ታውን የሚገኘው የዴዝሞን ቱቱ ኤችአይቪ ፋውንዴሽን መሪ ፕሮፌሰር ሊንዳ-ጌይል ቤከር ናቸው።
“በሽታ የመከላከል አቅም በተዳከመበት ሰው ላይ ቫይረሱ ሲቀጥል እናያለን:: ዝም ብሎ አይቀመጥም። ራሱን ያባዝል። ራሱን እያባዛም ይለወጣል። ይህም ለብዙ ወራት የሚቀጥል ነው” ብለዋል።
በጥናታቸው ወደፊት ቢገፉበትም ሳይንቲስቶቹ በዓለም ትልቁ የኤችአይቪ ወረርሽኝ ያለባት አገር በሆነችው በደቡብ አፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም ኤችአይቪ በደማቸው ያሉ ሰዎች ተጨማሪ መገለል እንዳይደርስባቸው ይሰጋሉ።
- አዲሱ ኮሮናቫይረስ ኦሚክሮን ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
- የዓለም ጤና ድርጅት በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት አገራት እንዳይደናገጡ አሳሳበ
- ኦሚክሮን፡ በፍጥነት በሚዛመተው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ምን ይሆናሉ?
“የፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች በሽታ የመከላከል አቅማቸው እንደሚመልስ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰር ቤከር።
በደቡብ አፍሪካ ሆስፒታሎች ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚስቡ ሁለት ጉዳዮች ተገኝተዋል። አንዲት ሴት እየተጠናቀቀ ካለው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ለስምንት ወራት ያህል የኮቪድ-19 ምርመራ ስታደርግ ቫይረሱ እንዳለባት እየተነገራት የቆየች ሲሆን ቫይረሱ ከ30 በላይ የዘረመል ለውጦችን አድርጓል።
የኦሚክሮን መኖርን ያረጋገጠውን ቡድን የመሩት ፕሮፌሰር ቱሊዮ ዴ ኦሊቬራ በበኩላቸው እንግሊዝን ጨምሮ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከ10 እስከ 15 ተመሳሳይ ጉዳዮች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
“በጣም አልፎ አልፎ የሚገጥም ክስተት ነው። የበሽታ መቋቋም አቅም የሌላቸው ግለሰቦች… የቫይረስ ዝግመተ ለውጥ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አሳማኝ ማሳያ ነው።”
የደቡብ አፍሪካ ሳይንቲስቶች በቅርቡ ኦሚክሮንን ማግኘታቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚሰነዘር ትችት አልፎ የግድያ ዛቻ ገጥሟቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ከምዕራባውያን አገራት ፈጣን፣ አወዛጋቢ እና ኢኮኖሚ የሚጎዳ የጉዞ እገዳዎችን ማስከተሉ ነበር።
አገራት ወይም አህጉሪቱ አዳዲስ ዝርያዎች መፈጠሪያ ሆነው ተለይተው መቅረብ አለባቸው የሚለውን ማንኛውንም ሃሳብ ቀድመው መከላከል ይፈልጋሉ።
የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች እና አዲስ የኮቪድ ዝርያዎች መካከል ያለው ግንኙነት “በጣም አሳማኝ መላምት ነው” ሲሉ ዋና የኤችአይቪ ስፔሻሊስት እና የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የኮቪድ-19 አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ሳሊም ከሪም ተናግረዋል።

“ነገር ግን አልተረጋገጠም። ከአራት የተለያዩ አህጉራት አምስት ዝርያዎች ሲመጡ አይተናል። ስለዚህ አፍሪካ ላይ ማሳበብ አናዳጅ ነው።”
ፕሮፌሰር ካሪም አክለውም “በሌላው ዓለም በሽታ የመከላከል አቅማቸው ስለተዳከመ ሰዎች አንጨነቅም። እኛ የምንጨነቀው ጥቁር ከሆኑ እና ከአፍሪካ የመጡ ከሆነ ብቻ ነው እንደማለት ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ካሪም አክለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች ለምን የበሽታ የመከላከል ሥርዓታቸው ይዳከማል ለሚለው የሳይንስ ሊቃውንት ሌሎች በርካታ ምክንያቶች እንዳሉም ያወሳሉ።
ለምሳሌ አልፋ የተባለው ዝርያ የመጣው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ የካንሰር ህክምና ከሚከታተል ታካሚ ጋር ተያይዟል።
በኬፕ ታውን ግሩት ሹር ሆስፒታል የተላላፊ በሽታዎች ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ማርክ ሜንዴልሰን “የስኳር በሽታ፣ ካንሰር፣ ረሃብ፣ ሥር የሰደደ ቲቢ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና በሌሎች ምክንያቶችም የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች አሉ” ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት መድኃኒት አይወስዱም።
ከኬፕ ታውን በስተደቡብ በምትገኘው በማሲፉሜሌሌ ከተማው ውስጥ ካሉ ጎልማሶች ሩብ ያህሉ ኤችአይቪ አለባቸው ተብሎ ይገመታል።
“ብዙ ጉዳዮች አሉ። አንዳንድ ሰዎች መመርመር አይፈልጉም። አንዳንዶች ማወቅ አይፈልጉም። በኤችአይቪ ዙሪያ መገለል አለ” ሲል የ25 ዓመቱ የማኅበረሰብ ሠራተኛው አሲፌ ንሾንጎትሺ ምክንያቱን አስቀምጧል።
- በቀጣይ በዓለም ላይ የሚከሰቱ ወረርሸኞች ከኮቪድ በላይ ገዳይ ሊሆኑ ይችላሉ ተባለ
- ለገና በዓል የሚኖረው እንቅስቃሴ የአዲሱን ቫይረስ መስፋፋት ሊያባብሰው ይችላል ተባለ
- ኦሚክሮን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተሰራጨ ነው- የዓለም ጤና ድርጅት
ምንም እንኳን ውጤታማ የጤና ፕሮግራም ቢኖርም በከተማዋም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የመድኃኒት ማዘዣ አልወሰዱም።
በአሁኑ ጊዜ ካሉት የኮቪድ ዝርያዎች መካከል አንዳቸውም በአፍሪካ ውስጥ መከሰታቸውን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። በድንገት ደቡብ አፍሪካ የደረሰው እንደ ኦሚክሮን ዓይነት ዝርያ መምጣቱ የበሽታ መከላከል ሥርዓቱ ከተዳከመ ሰው ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዲጨምር አድርጓል።
ቫይረሱን የሚከታተሉ ሳይንቲስቶች በአንዳንድ አካባቢዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከኤችአይቪ ጋር የሚደረገውን ትግል ችላ በተባለበት በዚህ ወቅት፣ ከኤችአይቪ ጋር ሊኖረው ይችላል የሚለው ስጋት ዓለም አቀፋዊ እርምጃ እንዲወስድ ያደርጋል ብለው ተስፋ አድርገዋል።
“ይህ ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው። ይህ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ እንዴት እንደሚስፋፋ መረዳት አለብን። በአሁኑ ጊዜ ያለን ምርጡ መከላከያ ክትባት ነው። ይህ መልዕክት ግልጽ መሆን አለበት” ብለዋል ፕሮፌሰር ቤከር።
አፍሪካ በኮቪድ-19 ክትባቶች ከተቀረው ዓለም ወደ ኋላ ቀርታ ብትገኝም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎች በተለይ የበሽታ መከላከል ሥርዓታቸው የተዳከመባቸው ሰዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ። የበሽታ መከላከያ አቅም እንዲኖራቸው እነዚህ ሰዎች አራት ወይም አምስት ዙር ክትባት ሊያገኙ ይገባል ይላሉ።
“የአዳዲስ ዝርያዎች መፈጠር አደጋን ለመቀነስ ከፈለግን ይህንን ኃላፊነት በዓለም ዙሪያ ባሉ በሁሉም አገሮች ውስጥ መውሰድ አለብን። ይህ ማለት በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ መከተባቸውን እና የበሽታ መከላከያ ምላሾች እንዲኖራቸው ለማድረግ መሞከር ነው።
“ካልሆነ የበሽታ መከላከል አቅም እስኪያገኙ ድረስ ተጨማሪ ክትባት ማግኘት አለባቸው። የበሽታ መቋቋም መዳከም ያለባቸው ሰዎች አዳዲስ ዝርያዎችን እዳያዳብሩ ይህ ለእኛ የተሻለው መከላከያ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰር ካሪም።