22 ታህሳስ 2021, 11:50 EAT

በኢትዮጵያ በ24 ሰዓታት ውስጥ በተደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተገለጸ።
በየዕለቱ የሚደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎችን መሠረት በማድረግ ማክሰኞ ታኅሣሥ 13/2014 ዓ. ም በጤና ሚኒስቴር በኩል የወጣው መረጃ እንዳመለከተው 2,323 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ይህ አሐዝም ከዚህ በፊት በአንድ ቀን ከተመዘገቡት በጣም ከፍተኛው ነው።
በየዕለቱ በ24 ሰዓት ይፋ የተደረጉ ቀደም ያሉ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ዕለታዊ አሐዝ ከ500 እስከ 1000 ባለው መካከል የቆየ ነበር።
- ኦሚክሮን፡ በፍጥነት በሚዛመተው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ምን ይሆናሉ?
- በአዲሱ የኮቪድ ዝርያ እና ህክምና ባላገኙ የኤችአይቪ ህሙማን መካከል ያለ ግንኙነት
- እስራኤል አራተኛ ዙር የኮቪድ ክትባት በመስጠት በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ልትሆን ነው
የማክሰኞ ዕለቱ ሪፖርት እንዳመለከተው 2,323 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው በዕለቱ ምርመራ ካደረጉ 10,016 ሰዎች መካከል ነው።
እስካሁን በአገሪቱ በወረርሽኙ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 379,379 የደረሰ ሲሆን፣ ትናንት ለተመዘገበው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ምክንያቱ ምን እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር እስካሁን የሰጠው መረጃ የለም።
እስካሁን በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከነበሩ መካከል 351,168 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ 6,877 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በዓለም ዙሪያ ክትባት እየተሰጠ ቢሆንም፤ በቅርቡ የተከሰተው ኦሚክሮን የተባለው አዲስ ዓይነት ዝርያ የበሽታውን የመስፋፋት ፍጥነትና አደገኝነት እንዳባባሰው የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
ይህ መጀመሪያ ላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መገኘቱ የተነገረው ኦሚክሮን በርካታ ሰዎች ላይ እየተገኘ ሲሆን አገራት በሽታውን ለመቆጣጠር ጥብቅ እርምጃ እየወሰዱ ነው።
ይህ የወረርሽኙ ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመገኘቱ በጤና ባለሥልጣናት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።