ከ 4 ሰአት በፊት

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ኦሚክሮን በተሰኘው ልውጥ የኮቪድ ዝርያ ላይ ቀደም ብሎ የተደረገ ጥናት አዲሱ ቫይረስ ከባድ ህመም የማስከተል እድሉ ቀደም ሲል ከነበሩት የኮቪድ ዝርያዎች ያነሰ መሆኑን አመለከተ።
ጥናቱ የተሰራው በደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ሲሆን እስካሁን በሌሎች ተቋማት አልተገመገመም።
ተቋሙ በጥናቱ በደቡብ አፍሪካ ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት አንድ እስከ ኅዳር 30 በኦሚክሮን ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በዚሁ ወቅት በሌሎች የቫይረሱ ዝርያዎች ከተያዙ ሰዎች ጋር ሲሲነጻጸር ታመው ሆስፒታል የመግባታቸው እድላቸው 80 በመቶ ያነሰ መሆኑን አመልክቷል።
ነገር ግን አንዳንድ የጥናቱ ግኝቶች በክትባት እና ቀደም ሲል በተከሰቱ ወረርሽኞች ሳቢያ የወል በሽታ የመከላከል አቅም ያዳበሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ አጥኚዎቹ የገለጹ ሲሆን ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን ቀደም ሲል በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ይገመታል።
- በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ቻይና በአንዲት ከተማ ላይ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች
- በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተመዘገቡ
- ኦሚክሮን፡ በፍጥነት በሚዛመተው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ምን ይሆናሉ?
የብሔራዊ የተላለፊ በሽታዎች ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሸሪል ኮኸን “የእኛ መረጃ ኦሚክሮን ከሌሎች ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸር የሚያስከትለው ህመም ያነሰ መሆኑን በአዎንታዊ መልኩ ይጠቁማል ” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰሯ አክለውም “እስካሁን ግልጽ ያልሆነው በከፍተኛ ሁኔታ ክትባት በተሰጡባቸው ግን ደግሞ ዝቅተኛ ቁጥር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ካሉባቸው አገራት ጋር ተመሳሳይ መሆን አለመሆኑ ነው” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የወጣ ጥናት ምንም እንኳን ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ውስን ቢሆንም እንዲሁም ጥናቱ በሌሎች ባይገመገምም የኦሚክሮን ልውጥ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ከደልታ ዝርያ ቀላል ህመም ማስከተሉን የሚያመላክት መረጃ አለመኖሩን ገልጿል።