ከ 2 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ በያዝነው ሳምንት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፤ አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ኦሚክሮን ገብቶ ከሆነ ለማረጋገጥ የናሙና ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ለቢቢሲ ገለጹ።
ባለፈው ሳምንት ከተመረመሩ 53 ሺህ ሰዎች መካከል 8500 በቫይረሱ ሲያዙ፣ 34 ሰዎች ሞተዋል። በተጨማሪም 440 ሰዎች የጽኑ ሕሙማን ክፍል ገብተዋል።
ካለፉት ሳምንታት በተለየ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፤ ኦሚክሮን ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ መሆኑን ለማወቅ የናሙና ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝና ውጤቱ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ዶ/ር ደረጄ ተናግረዋል።
“እስካሁን የነበረው አካሄድ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ከታኅሳስ 7/2014 ዓ. ም. ወዲህ ባሉት ቀናት በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው” ብለዋል።
የዛሬ ሳምንት ገደማ ከሚመረመሩ ሰዎች 3% ብቻ ቫይረሱ ይገኝባቸው የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ግን ቁጥሩ ወደ 28% እንዳደገ ገልጸዋል።
- ከጉንፋን መሰል ሕመሞች ግማሹ ኮሮናቫይረስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ
- በአውስትራሊያ በአፍንጫ የሚወሰድ የኮቪድ-19 መከላከያ ላይ ሙከራ እየተደረገ ነው
- ኦሚክሮን የሚያስከትለው ህመም ቀላል መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የተደረገ ጥናት አመለከተ
- በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተመዘገቡ
“በሌሎች አገሮች የሚታየው ኦሚክሮን ዝርያ በኢትዮጵያም ምልክቶቹ ታይተዋል። በአስጊ ሁኔታ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። አሁን ናሙና እየመረመርን ነው። በናሙና እስክናረጋግጥ ድረስ ኦሚክሮን መግባቱን በይፋ ለመናገር ያስቸግራል” ሲሉ ዶ/ር ደረጄ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመርምረው 382 ሺህ ቫይረሱ ሲገኝባቸው፤ 6880 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ወደ 10 ሚሊዮን ገደማ ዜጎችን ከትባለች።
ዶ/ር ደረጄ እንዳሉት፤ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ዜጎች ክትባት እንዲወስዱ ከማበረታታት ባሻገር ከዚህ ቀደም የተከተቡ ሰዎች ማጎልበቻ (ቡስተር) እንዲወስዱ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
ከ100 በላይ አገሮች ውስጥ የተገኘው የኦሚክሮን ዝርያ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ ነው።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ትናንት ከተመረመሩ 13147 ሰዎች መካከል 3793 ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ጤና ሚኒስትር ገልጿል።
“በቫይረሱ በድጋሚ የመያዝ ዕድል አለ። ማኅበረሰቡ ወረርሽኙ ‘ውሸት ነው’ ወይም ‘ለፖለቲካ ነው’ ሳይል ክትባት ይውሰድ። ስለ ክትባት ሐሰተኛ ወሬ ማሰራጨት ያቁም። ከዚህ ቀደም እንደነበረው ለሕሙማን አልጋ የጠፋበት ደረጃ እንዳንደርስ ተጠንቀቁ” ሲሉ አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስቴር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል፤ የጤና ባለሙያዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ክትባት እንዲወስዱ ማድረግ እንዲሁም ያልተከተቡ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የመንግሥት የነጻ ሕክምና ተጠቃሚ እንይሆኑ ማድረግ መሆኑን ዶ/ር ደረጄ ጠቅሰዋል።
“አሁን ላይ ከሚመረመሩት ሰዎች አንድ ሦስተኛው ቫይረሱ እየተገኘባቸው ስለሆነ የጥንቃቄ እርምጃ መወሰድ አለበት። ማኅበረሰቡ ማስክ ማድረግ፣ ክትባት መከተብም ይገባዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የጤና ሚኒስቴር የወረርሽኙን ስረጭት ለመከላከል የሚያወጣቸውን ሕጎች በማስተግበር ረገድ ሕግ አስፈጻሚው አካል ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።
በተጨማሪም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማኅበረሰቡ እንዲተገብር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እስከ ቀበሌ የሚወርድ ንቅናቄ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ለገና በዓል ከሚመጡ ዳያስፖራዎች ጋር በተያያዘ የምርመራ ውጤት እና የክትባት ሰርተፍኬት ከማረጋገጥ አንስቶ ክትባቱን አገር ውስጥ እስከማቅረብ ድረስ እንደሚዘጋጁ ዶ/ር ደረጄ ተናግረዋል።