ከ 7 ሰአት በፊት

Man blowing nose on tissue

መቼም ሰሞኑን እርስዎ ወይም በቅርበት የሚያውቋቸው በርካታ ሰዎች ‘በኃይለኛ ጉንፋን’ ተይዘው ትኩስ ነገር ሲወስዱ ተመልከተዋል። ሌሎችም ከወረርሽኙ ራሳቸውን ለመታደግ መፍትሔ ያሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።

ይህ ጉንፋን መሰል ሕመም በርካቶችን ይዞ አንዳንዶችን በከባድ ህመም አሰቃይቶ ቢያልፍም፣ ሌሎችን ክፉኛ አጎሳቁሎ አልጋ ላይ አውሏቸው የጎዳቸው ስዎችም አሉ።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የመያዝ ምጣኔው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እያሻቀበ ይገኛል። ለነገሩ ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ እየተስተዋለ ይገኛል።

ልዩነቱ የተለያዩ አገራት በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ለማደጉ ምክንያት የሚያደርጉት ኦሚክሮን የተሰኘውን አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያን ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም ዙሪያ ኦሚክሮን ከተከሰተ በኋላ በቫይረሱ የሚያዙ ስዎች ቁጥር በየሁለት ቀኑ በእጥፋ ያድጋል። በአሜሪካ ብቻ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ13 በመቶ ወደ 73 በመቶ ከፍ ብሏል።

በኢትዮጵያ የኦሚክሮን ዝርያ መኖሩ በጤና ሚኒስቴር በኩል በይፋ ባይረጋገጥም በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ግን ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ ነው።

ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው የጤና ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ “የኦሚክሮን ዝርያን የሚመስሉ ምልክቶች” እታዩ እንደሆነ እና ቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ ተናግረዋል።

Presentational grey line

የሰሞኑ ጉንፋን የሚያስከትለው ሕመም

Presentational grey line

የሰሞነኛው ‘ጉንፋን’ ምንድን ነው?

ቢቢሲ ያናገራቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒም ሆስፒታል እና ሜዲካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር እና የህጻናት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ፋሲል መንበረ፣ በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች በዚህ ጉንፋን መሰል በሽታ ለመያዛቸው በምክንያትነት የሚያስቀምጡት የጥንቃቄ ጉድለትን ነው።

“ብዙ ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አያደርግም። በበርካታ ምክንያቶች የሰዎች በአንድ ስፍራ መሰባሰብና ንክኪ እንዳለ ነው። በሽታውን [ኮሮናን] ጭራሽ የመርሳት ነገር ይሰተዋላል” የሚሉት ዶክተር ፋሲል የትምህርት ቤት መከፈት እና የተማሪዎች እንቅስቃሴም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጥንቃቄ የጎደለው የሰዎች መሰባሰብና ንክኪ መበራከትና የእንቅስቃሴ መጨመር ‘ለሰሞነኛው ህመም’ ከሰዎች ወደ ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት እንዲዛመት አድርጓል።

ይህ በሽታ ኮሮናቫይረስ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው የሚሉት ዶክተር ፋሲል በሽታው የተለየ ባህሪ አለው ለማለት ጥናት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

ሆኖም “ስዎች ያሁኑ ገንፋን እያሉ የሚጠሩት ለየት ያለ ነገር” ጠንከር ያለ ሳል፣ ጠንከር ያለ ተኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የወገብ ህመም፣ ቁርጥማት የማሽተት እና የማጣጣም ስሜትን ማሳጣት መገለጫዎ እንደሆኑ ታማሚዎች ደጋግመው መግለጻቸውን ያስረዳሉ።

“ኮቪድም ከኮቪድ ውጪም ያሉ ቫይረሶች እንደዚህ አይነት ምልክቶች ያስከትላሉ። ነገር ግን ከሌላው ጊዜ የሚለው ይሄ ቫይረስ ብዙ ስዎችን መያዙ እና ጠንከር ያሉ ምልክቶች መሳየቱ ነው። ምን አልባት እንዚህ ምልክቶች ሁሉም ሰው ወደ ሆስፒታል እንዲሄድ ላያደርጉት ይችላሉ። ብዙ ስዎች በቤት ውስጥ እያገገሙ እንዳሉ መረጃዎች አሉን።”

Presentational grey line

የመከላከያ መንገዶች

Presentational grey line
አፏን ሸፍና የምታስል ሴት

በሽታው ማን ላይ ይከፋል?

እድሜያቸው ከሦስት ወር በታች የሆኑ ህጸናት እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውን አዋቂ ሰዎች ይህ ሰሞነኛ በሽታ ክፉኛ ሊጎዳቸው እንደሚችል የሚጠቅሱት ዶክተር ፋሲል፣ ለምሳሌ ሰኳር፣ የደም ግፊት እንደዚህ የመሳሰሉ ተጨማሪ ህመም ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ ወደ ከፋ ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ።

በተለይ “ከሦሰት ወር በታች ያሉ ህጻናት ደግሞ የአየር ቧንቧቸው እና አፍንጫቸው በጣም ጠባብ ስለነ እዚያ በቀላሉ የመታፈን፣ ለመተንፈስ የመቸገር፣ የመጨናነቅ እና እስከ ሆስፒታል ደረጃ ሊያደርሳቸው ስለሚችል ለእነሱ ጠንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።”

የህጸናት ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶክተር ፋሲል ጨምረውም “በተለይ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሌሎች ህጻናት ወደ ጨቅላዎቹ በሽታውን ወይም ቫይረሱን ይዘው እንዳይመጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ስዎችም በበሽታው ከፍ ላለ የመተንፈስ ችግር ሊዳርጉ እንደሚችሉም አንስተዋል።

በመሆኑም የትንፋሽ ማጠር ወይም ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ ከፍተኛ ትኩሳት እና መድከም ካለ ምን አልባት በሽታው የከፋ ደረጃ መድረሱን አመላካች ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

Presentational grey line

ለልጆችና ለህፃናት የቤት ውስጥ ሕክምና

Presentational grey line

በሽታውን እንዴት መከላከል እና ማከም ይቻላል?

እንደዚህ አይነት በሽታዎች መነሻችው ቫይረስ እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶክተር ፋሲል ቀድም ሲል የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንሚረዱ የተገለጹ እርምጃዎችን ማለትም አፍና የአፍነጫ መሸፈኛን በአግባቡ መጠቀም፣ የእጅን ንጽህና መጠበቅ፣ ከመሰባሰብ መቆጠብ በበሽታው የመያዝ ዕድልን እንደሚቀንሱ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የኮሮናቫይረስ ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት መውሰድ ለዚህ በሽታ የመጋለጥ እድልን ለማጥበብም ይረዳል ብለዋል ዶ/ር ፋሲል።

ይህንን ህመም ለመከላከል በሚል በሐኪም ካልታዘዘ በስተቀር ፀረ ባክቴሪያዎችን ወይም አንቲባዮቲክስን መወሰድ በፍጹም ተገቢ እንዳልሆነ መክረዋል።

“ለምሳሌ አሞክሳሲሊን፣ አዚትሮማይሲን፣ ኦግመንቲን የሚባሉ አንቲባዮቲክሶች አለመጠቀም ነው ሚመከረው። ለምን? እነዚህ ባክቴሪያ እንጂ ቫይረስ የሚያጠፉ መድኃኒቶች ስላልሆኑ ሐኪም እስካላዘዘልን ድረስ መጠቀም የለብንም።”

ከዚህ ባሻገር በበሽታው የተያዙ ጨቅላ ህጻናት በቤት ውስጥ ለማከም ‘ለብ ያለ’ ውሃ በጨው አድርጎ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በጠብታ መልክ በአፍንጫው መስጠት እንዲሁም የአፍንጫ ንጽህናቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ታዲጊዎች ደግሞ በቂ እረፍት መውሰድን ጨምሮ እንደ ነጭ ሽንኩርት፣ ማር፣ ዝንጀብል ያላቸውን ምግቦች መመገብ የበሽታ መከልከል አቅምን በማሳደግ በሽታውን ለመቋቋም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

“ነጭ ሽንኩርት አንዳንድ ቫይረሶችን የመቆጣጠር ባህሪይ እንደሚያሳይ በሳይንስም የተረጋገጠ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል ለአዋቂዎችም ይሁን ለህጻናት ከሰውነታቸው የሚያስወጡትን ፈሳሽ ለመተካት ትኩስ ነገሮችን መጠጣት፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

Presentational grey line

ለታዳጊዎችና ለአዋቂዎች የቤት ውስጥ ሕክምና

Presentational grey line
Woman coughing

የሥነ ምግብ ባለሙያ

ከዚህ በፊት በጉንፋን የተያዙበትን ጊዜ የማያስታውሱት የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ሼፍ አዲስ ዓለም ብዙአየሁ፣ በሰሞኑ ጉንፋን መሰል በሽታ ተይዘው እንደነበር ይናገራሉ።

ሰውነታችን ለእንዲህ አይነት በሽታ የሚጋለጠው ወይም ከተጋለጠ በኋላ የከፋ ሕመምና ጉዳት የሚደርስበት የበሽታ መከላከል አቅም ሳይዳብር ወይም ሲዳከም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሰውነት በሽታ የመከላክል አቅምን ለማሳደግ ደግሞ አዘውትሮ አትክልት እና ፍራፍሬን መመገብ ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነና ይህም ወቅት ለሚያመጣቸው በሽታዎች በቀላሉ ‘እጅ’ ላለመስጠት ያግዛል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሰሞነኛው በሽታ የተያዙ ደግሞ የአትክልት ሾርባዎችን፣ እንደ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ ኑግን የመሳሰሉ የቅባት እህሎችን ከትኩስ መጠጦች ጋር መውሰድ ከበሽታው በፍጥነት ለማገገም ይረዳል።