ከ 6 ሰአት በፊት

በታይላንድ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ

የኮሮናቫይረስ ዴልታ እና ኦሚክሮን የተሰኙት ልውጥ ዝርያዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን በማበራከት አደገኛ ማዕበል እያመጣ ነው ሲሉ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ገለፁ።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ይህንን ያሉት በአሜሪካ እና በመላው አውሮፓ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን መመዝገባቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

ፈረንሳይ 208 ሺህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለሁለት ተከታታይ ቀናት በመመዝገብ በአውሮፓ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛውን ዕለታዊ አሃዝ አስፍራለች።

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በአማካይ በቀን 265 ሺህ 427 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መመዝገቧን ጆንስ ሆፕኪንስ አሳውቋል። በሌላ በኩል ዴንማርክ፣ ፖርቹጋል፣ እንግሊዝ እና አውስትራሊያ ታይቶ የማይታወቅ አሃዞችንም መዝግበዋል።

ትላንት ረቡዕ ፖላንድ 794 በኮቪድ የተያያዙ ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርት ያደረገች ሲሆን ይህም በአራተኛው የወረርሽኙ ማዕበል ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር ነው። ከሟቾች ውስጥም ከሶስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት ያልተከተቡ ሰዎች እንደነበሩ ተመላክቷል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኦሚክሮን በፍጥነት በብዙ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳረፈ ሲሆን እንደ ዴልታ ዝርያ የከፋ ባይሆንም በከፍተኛ ፍጥነት ይዛመታል።

ዶክተር ቴድሮስ ለወረርሽኙ መበራከት የሁለቱ ዝርያዎች “ጥምር” ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ኃላፊው አክለውም ሁኔታው ” በተዳከሙ የጤና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር እና የጤና ስርአቶችን ሊያናጋው ይችላል” ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በየቀኑ ወደ 900 ሺህ የሚጠጉ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየተዘገቡ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ተላላፊ በሽታ ባለሙያው የዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ለ ሲኤን ኤን ሲናገሩ የኦሚክሮን ዝርያ በአሜሪካ በቀጣዩ ወር መጨረሻ ካለው የሕዝብ ብዛት እና ከክትባት መጠኑ አንፃር ከፍተኛ ጫፍ ላይ ሊያደርስ እንደሚችሉ ተናግረዋል ።

የተለያዩ ሃብታም ሀገራት ሶስተኛ ዙር ክትባት ወይም ማጠናከሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ሆኖም ዶ/ር ቴድሮስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የበለፀጉ አገራት መጠነ ሰፊ የማጠናከሪያ ክትባት ዘመቻዎች “ወረርሽኙን እንዲራዘም” ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለዋል። ምክንያቱም የክትባት አቅርቦቶችን ከድሃ ሀገራት በማዘዋወሩ ቫይረሱ “እንዲሰራጭ እና አዳዲስ ዝርያ እንዲፈጥር የበለጠ እድል ይሰጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

“እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 አጋማሽ 70 በመቶ የሚሆነውን የአለም ህዝብ ክትባት እንዲያገኝ የተጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ ሁሉም ሰው መከተብን የአዲስ አመት ዕቅድ እንዲያደርገው ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ወደ 100 የሚጠጉ ሀገራት 40 በመቶ የሚሆነውን ህዝቦቻቸውን የመከተብ የመጀመሪያ ግብ ገና እንዳላሳኩም የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል።

ከቀናት በፊት የወጣ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው እንደ አውሮፓውያኑ ከታህሳስ 26 በፊት በአውሮፓ ሁሉም ዓይነቶች አዲስ የኮቪድ ዝርያዎች ቁጥር በ57 በመቶ በአሜሪካ ደግሞበ በ30 በመቶ አድጓል።

የጤና አስተዳደር ሃላፊዎች ለአንዳንዶቹ ከፍተኛ አኃዞች መመዝገብ በከፊል በገና በዓል ምክንያት ይፋ የሚየያደርጉት ዘግይቶ ስለሆነ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል