31 ታህሳስ 2021

ክትባት

የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ በሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የኮሮናቫይረስ ክትባት ስርጭት በሁሉም የአፍሪካ አገራት ቢያንስ 40 በመቶ እንዲደርስ ያስቀመጠው ግብ ሳይሳካ ቀረ።

ድርጅቱ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ ይህ ዕቅድ እንደሚሳካ በማሰብ ቢያስቀምጥም ማሳካት የቻለው ግን በጣም አነስተኛ ቁጥር ነው።

እስካሁንም በአጠቃላይ ከአፍሪካ ሙሉ በሙሉ የተከተበው ሕዝብ ቁጥር 9 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።

ነገር ግን ሰባት አገራት ብቻ የዓለም ጤና ድርጅትን ግብ ማሳካት ችለዋል። ሲሸልስ እና ሞሪሺየስ ከ70 በመቶ በላይ ሕዝባቸውን ሁለት ዙር ክትባት የሰጡ ሲሆን ኬፕ ቬርዲ ደግሞ ወደ 45 በመቶ የሚጠጋው ሕዝቧ ሁለት ዙር ክትባቱን እንዲያገኝ አድርጋለች።

በተጨማሪ ደግሞ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ቦትስዋና እና ሩዋንዳ የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ዕቅድ ማሳካት የቻሉ አገራት መሆናቸው ተገልጿል።

በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ አገራት ክትባትን ለሕዝባቸው ከማዳረስ አንጻር ከሰሀራ በታች ካሉት አገራት አንጻር የተሻለ አፈጻጸም አሳይተዋል።

በአጠቃላይ ደግሞ አሮጌው ዓመት 2021 ከመጠናቀቁ በፊት ከአፍሪካ አገራት ግማሽ የሚሆኑት ብቻ ከ10 በመቶ በላይ ሕዝባቸውን ሁለት ዙር መከተብ ችለዋል።

በአህጉሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር በመያዝ የምትመራው ናይጄሪያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከአጠቃላይ ሕዝባቸው ከ5 በመቶ በታቹን ነው መከተብ የቻሉት።

በናይጄሪያ በአጠቃላይ 2.1 በመቶ ሕዝቧን የከተበች ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ 3.5 በመቶ ሕዝቧን ነው መከተብ የቻለችው።

ክትባት የያዘች የጤና ባለሙያ

ሌላኛዋ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ መከተብ የቻለችው ከአጠቃላይ ሕዝቧ 0.1 በመቶውን ብቻ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት 2022 በመላው አፍሪካ 70 በመቶ የክትባት ሽፋን ለማድረስ ያቀደ ቢሆንም የሚጠናቀቀውን ዓመት አፈጻጸም በማየት የመሳካት ዕድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው።

“አሁን ክትባቶች እየደረሱ ባለበት ፍጥነት ይህንን ዕቅድ ማሳከት የምንችለው ምናልባት በነሐሴ ወር 2024 ሊሆን ይችላል” ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ማሺዲሶ ሞዌቲ።

ደካማ የጤና መሠረተ ልማት፣ ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ዝቅተኛ መሆን፣ የገንዘብ እጥረት እንዲሁም ክትባት የማቆያ መጋዘኖች እጥረት ለዓለም ጤና ድርጅት ዕቅድ አለመሳካት እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሱ ማነቆዎች ናቸው።

የአፍሪካ ተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደሚለው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ አፍሪካ የሚመጡት ክትባቶች በጣም አጭር የቆይታ ጊዜ ያላቸው ናቸው።

ክትባቶች ሳይበላሹ ቢያንስ ለሁለት ወራት መቆየት የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን አገራትም ቢሆን ክትባቶቹ ከመላካቸው በፊት የአንድ ወር ቅድመ መረጃ ሊደርሳቸው ይገባል። በአፍሪካ ግን ይህ እየሆነ አይደለም።

የአፍሪካ አገራት ክትባቶቹን በብዛት የሚያገኙት ከድጋፍ ሰጪ አገራት፣ ኮቫክስ የተሰኘውና ክትባት ለደሃ አገራት እንዲደርስ የተመሠረተው ዓለም አቀፍ ጥምረት በኩል ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናቸው።