10 ጥር 2022, 16:07 EAT

አፍንጫዋን በጨርቅ የሸፈነች ሴት

ጉንፋን ከያዘን በኋላ በተፈጥሮ የምናዳብረው የበሽታ መከላከያ ከኮቪድ-19ም ሊከላከል እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

ይህንን ያመለከተው ውስን መጠን ባላቸው ሰዎች ላይ የተካሄደ ጥናት ሲሆን፤ በዚህም በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ጋር በኖሩ 52 ሰዎችን ላይ ክትትል ተደርጎ የተገኘው ውጤትም ‘ኔቸር ኮሚዩኒኬሽን’ በተባለው መጽሔት ላይ ታትሟል።

በጥናቱ ከተካተቱት መካከል ጉንፋን ከያዛቸው በኋላ ሰውነታቸው በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ ህዋሳትን ለማነቃቃት የሚረዳ የማስታወስ ብቃት ያዳበሩት በኮቪድ የመያዝ ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተመልክቷል።

ነገር ግን ባለሙያዎች ማንም ሰው በዚህ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ መንገድ ላይ ብቻ መተማመን እንደሌለበትና መከተብ ቁልፍ መፍትሔ መሆኑን አስምረውበታል።

ቢሆንም በጥናቱ የተገኘው ውጤት የሰውነታችን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል ሥርዓት ቫይረሱን እንዴት እንደሚዋጋ ለመረዳት የሚያግዝ በጣም ጠቃሚ መረጃን አስገኝቷል ብለዋል።

ኮቪድ-19 የሚከሰተው በአንዱ አይነት የኮሮናቫይረስ አማካይነት ሲሆን አንዳንድ የጉንፋን በሽታዎችም የኮሮናቫይረስ ዝርያ በሆኑ ሌሎች ቫይረሶች የሚከሰቱ ናቸው። በዚህም አንደኛውን ለመከላከል የሚገኝ በተፈጥሯዊ መከላከያ ሌላኛውንም መከላከል ይችል እንደሆነ እየመረመሩ ነው።

ሁሉም የጉንፋን ህመሞች በኮሮናቫይረስ አማካይነት የሚከሰቱ ባለመሆናቸው በቅርቡ በጉንፋን የተያዘ ሰው በኮሮና ሊያዝ አይችልም ብሎ ማመን “ትልቅ ስህተት” ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ባለሙያዎች መክረዋል።

ጥናቱ በዋናነት ያተኮረው የሰውነታችን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት ውስጥ በሚገኘው ‘ቲ’ በተሰኘው ህዋስ ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህ ህዋሳት አንዳንዶቹ በሰውነታችን ውስጥ ጉንፋንን በመሰለ በሽታ የተጠቁ ህዋሳትን ያስወግዳሉ።

እናም በጉንፋን ተይዘን ከዳንን በኋላ የተወሰኑ ‘ቲ’ ሴሎች በሰውነታችን ውስጥ በመቆየት የመከላከያ ሥርዓታችን በሽታውን እንዲያስታውስ አድርገው ወደፊት በሽታውን ለመከላከል አቅም እንዲኖረን ያግዛሉ።

ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ነበር ተመራማሪዎቹ በኮቪድ ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚኖሩ 52 ሰዎች ላይ ጥናታቸውን ያደረጉት። ከእነዚህ በበሽታው ካልተያዙት መካከል አንድ ሦስተኛዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ‘ቲ’ ህዋስ በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል።

ለዚህም ምክንያቱ ሰዎቹ ከዚህ በፊት በሰው ላይ በሚከሰት ሌላ አይነት የኮሮናቫይረስ በሆነው በጉንፋን በተያዙበት ጊዜ ይህንን የመከላከያ ሥርዓት አዳብረው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

ነገር ግን ከዚህ ባሻገር ተመራማሪዎቹ ሰዎቹ በቤታቸው ውስጥ ያለው የአየር ዝውውርና ከህሙማኑ ጋር የነበራቸው ንክኪም በበሽታው የመያዝ እድላቸውን እንደሚቀንሰው ተናግረዋል።