ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የኅብረቱን ጉባኤ በአካል በአዲስ አበባ ለማከናወን ያሳለፉትን ውሳኔ ኢትዮጵያ ታደንቃለች ብለዋል።
ዶ/ር ዐቢይ ፥ ” ወንድማዊ አጋርነታችሁን በምንሻበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የኮሮናን መስፋፋትንና ወቅታዊውን የጸጥታ ሁኔታ እንደ ምክንያት በማንሣት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት ተግባራቸው ኢትዮጵያን አሳዝኖ ነበር ” ብለዋል።
አክለው ፥ ” በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤያት መካከል በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የመጀመሪያው ጉባኤ ከ3 ዓመት በኋላ ዳግም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመሆን መንግስት ልዩ ልዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ” ሲሉ አስረድተዋል።
ዶክተር ዐቢይ፥ ” ጉባኤው እዚህ መካሄዱ የሚኖረውን ትርጉም የተገነዘቡና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም፣ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እና የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን እንዲታዩ ያላትን የጸና መርሕ ከፍ ያለ ዋጋ የሰጡ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱን መርጠዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ደስ ተሰኝታለች፤ እንኳን ደስ ያለን ” ሲሉ ገልፀዋል።