6 የካቲት 2022, 08:05 EAT

የጥንዶቹ ጉዞ መንገዶችን፣ ሕንፃዎችን እና ድልድዮችን ከሕዝብ የምራቅ ማዕበል ለመጠበቅ ያለመ ነው።
የምስሉ መግለጫ,የጥንዶቹ ጉዞ መንገዶችን፣ ሕንፃዎችን እና ድልድዮችን ከሕዝብ የምራቅ ማዕበል ለመጠበቅ ያለመ ነው።

በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ ራጃ እና ፕሪቲ ናራሲምሃን አንድ መልዕክት ይዘው በመላው ሕንድ ጉዞ ጀምረው ነበር።

መልዕክቱ ‘በየአደባባይ መትፋት አቁሙ’ የሚል ነው።

ጥንዶቹ በፀረ መትፋት መፈክሮች በተሸፈነ መኪና ሆነው በድምጽ ማጉያ መልዕክት ያሰሙ ነበር።

ወደ ሕንድ አቅንተው ጥቂት ቀናትን ካሳለፉ እነ ናራሲምሃን ምን እንደሚቃወሙ ይገለጥሎታል።

ሕንድ ጎዳናዎቿ በምራቅ ተሞልተዋል።

አንዳንዱ ንጹህ ሌላው ደግሞ ትምባሆ በማጨስ እና በተለያየ ምክንያት ደም የመሰለ ቀይ ነው።

ይህም በግድግዳዎችን እና ግዙፍ ሕንፃዎች ላይ ሳይቀር ይታያል። በካልካታ ከተማ የሚገኘው ታሪካዊ የሃውራ ድልድይም በዚህ ምክንያት አደጋ ተጋርጦበታል።

የጥንዶቹ ጉዞ መንገዶችን፣ ሕንፃዎችን እና ድልድዮችን ከሕዝብ የምራቅ ማዕበል ለመጠበቅ ያለመ ነው።

ነዋሪነታቸው ፑን ከተማ ነው። እአአ ከ2010 ጀምሮ መትፋትን ለመከላከል ራሳቸውን የሾሙ ነጻ አውጪዎች ሆነዋል።

ሥልጠናዎች፣ የበይነ መረብ ቅስቀሳዎች እና ከማዘጋጃ ቤቶች ጋር የማጽዳት ዘመቻዎችን ጨምሮ ሁሉንም ሞክረዋል።

ጥንዶቹን አንድ ጊዜ የገጠማቸው ግን ከሁሉም የተለየ ነው።

በፑን የባቡር ጣቢያ ግድግዳ ላይ ማስታወቂያ ይሰቅላሉ። ከሦስት ቀናት በኋላ ግን ነዋሪዎች ማስታወቂያው ላይ እንደገና ምራቅ ይተፉበት ጀመር።

“ግድግዳ ላይ የምንተፋበት ምንም ምክንያት የለም” ይላል ማስታወቂያው።

ለምክራቸው የተሰጠው ምላሽ ግን ከግድየለሽነት እስከ ቁጣ ይደርሳል።

ናራሲምሃን “አትትፉ የምትለን ለምንድን ነው? ይህ የአባትህ ንብረት ነው?” ብሎ የጠየቀውን አንድ ሰው ያስታውሳል።

ሕንድ ላይ ክንዱን ያበረታው የኮቪድ-19 ማዕበል አንዳንድ ነገሮችን ቀይሯል ትላለች ፕሪቲ። ከሚተፉት ሰዎች አንዳንዶቹም ይቅርታ ጠይቀዋል።

“የወረርሽኙን ፍርሃት እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል” ትላለች።

‘የምትተፋው አገር’

ሕንድ በጎዳናዎቿ ምራቅ እንዳይተፋ የምታደርገው ትግል ሁሌም በግማሽ ልብ የሚደረግ ነው።

ሙምባይ ሰዎች በአደባባይ እንዳይተፉ፣ ቆሻሻ እንዳይጥሉ ወይም እንዳይሸኑ በሚገስጹ በጎ ፈቃደኛ “አስጨናቂ” ተቆጣጣሪዎች ሞክራ ነበር።

ሆኖም መትፋት እንደ ጥፋት ሳይቆጠር ረዥም ጊዜ አልፏል።

በኋላም ኮቪድ-19 መጣ።

ባለሥልጣናት በአደጋ ጊዜ አስተዳደር ሕግ መሠረት መትፋትን በከፍተኛ ገንዘብ እና የእስር ጊዜ ጭምር በመቅጣት ወደ ተግባር ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲም የአገራቸው ሰዎች በየቦታው እንዳይተፉ መከሩ። “ስህተት እንደሆነ እናውቃለን!” ሲሉ ጭምር ገለጹ።

ይህ ሕግ እአአ በ2016 ከነበረው አመለካከት በእጅጉ ተቃርኖ ነበረው።

በወቅቱ ስለመትፋት ጥያቄ የቀረበላቸው የጤና ሚኒስትሩ ለአገሪቱ ፓርላማ ሲመልሱ “ጌታዬ፤ ሕንድ የምትተፋ አገር ነች። ሲደብረን እንተፋለን፣ ሲደክመን እንተፋለን፣ ስንናደድ እንተፋለን ወይም በሌላም በሌላም ምክንያት እንተፋለን። የትም ቦታ እንተፋለን። ሁልጊዜም፣ በማይጠበቅ ሰዓትም ጭምር እንተፋለን” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ትክክል ናቸው። የሕንድ ጎዳናዎች እና መትፋት ተጣብቀዋል።

በመንገድ ዳር ያሉ ወንዶች አልፎ አልፎ ጭንቅላታቸውን ጥቂት ሴንቲ ሜትር ዘወር አድርገው ይተፋሉ።

መኪናና ሳይክል የሚያሽከረክሩ ወንዶችም በትራፊክ መብራቶች ላይ አንገታቸውን ወጣ አድርገው ለመትፋት አያቅማሙም።

ልማዱ የወንዶች ነው። ከመትፋታቸው በፊት የሚጎረብጥ ድምጽ ከጉሮሯቸው ይሰማል።

ሕንዳውያን ወንዶች በሰውነታቸው ብቻ ሳይሆን “ከሰውነት በሚወጣ ሁሉ” ምቾት ይሰማቸዋል ይላል አምደኛው ሳንቶሽ ዴሳይ።

መኪናና ሳይክል የሚያሽከረክሩ ወንዶችም በትራፊክ መብራቶች ላይ አንገታቸውን ወጣ አድርገው ለመትፋት አያቅማሙም።
የምስሉ መግለጫ,መኪናና ሳይክል የሚያሽከረክሩ ወንዶችም በትራፊክ መብራቶች ላይ አንገታቸውን ወጣ አድርገው ለመትፋት አያቅማሙም።

“በአደባባይ በመትፋት ራስ ወዳድነታቸው ይታያል። በእውነቱ ራሳቸውን የመገደብ ሐሳብም የላቸውም።”

የሕንዱ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ተባባሪ አርታኢ የሆነው ኡዳላክ ሙከርጂ እንደሚለው መትፋት እንደወንድነት የሚቆጠር የ”አራድነት” ዓይነት ነው።

ለምን በአደባባይ ይተፋል?

ናራሲምሃን በአደባባይ ለመትፋት ምክንያቶቹ ቁጣ ወይም መትፋትን እንደ “ጊዜ ማሳለፊያ” መመልከት ነው ይላል።

መትፋት ስለቻሉ ብቻ መትፋት መብታቸው እንደሆነ የሚሰማቸውም አሉ።

ሙኩል ኬሳቫን የተባሉት የታሪክ ምሁር እንደሚሉት ደግሞ “ከሕንድ የብክለት አባዜ” የመነጨ ነው።

አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች ይህ አባዜ የቆሸሸን ማንኛውንም ነገር ከቤት በማስወጣት የሰውነት ንጽህናን ከመጠበቅ ጋር ይያያዛል ይላሉ።

ሙከርጂ እንዳለው የመትፋት አመለካከት ከንጽህና ጥያቄዎችም በላይ ነው።

“አንድ የታክሲ ሹፌር በአንድ ወቅት ‘ክፉ ቀን ስላሳለፍኩ ልምዴን ማውለቅ እፈልጋለሁ” ብሎኛል’ “ሲል ተናግሯል።

ከመትፋት ጋር የሚደረግ ጦርነት

ሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች በየቦታው የሚተፉበት ጊዜ ነበር።

በሕንድ ንጉሣዊ ፍርድ ቤቶች እና በብዙ ቤቶች ውስጥ ምራቅ መትፋት ያስከብር ነበር።

በመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ ምግብ እየተመገቡ ከጠረጴዛው ስር እስከሆነ ድረስ መትፋት ይችላሉ።

ኢራስመስ “ምራቅን መዋጥ ጨዋነት የጎደለው ተግባር” ነው ሲል ጽፏል።

የማሳቹሴትስ የጤና ተቆጣጣሪ በ1908 በጎበኟቸው ፋብሪካዎች ለምን መሬት ላይ እንደሚተፋ ሲጠይቁ “መሬት ላይ እንጂ የት እንዲተፋ ነበር የሚጠብቁት? ኪሳቸው ውስጥ ይትፉ?” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ዘግቧል።

በእንግሊዝም ተመሳሳይ ነገር ነበር።

ሰዎች በመኪኖች ላይ መትፋታቸው የተለመደ በነበረበት ወቅተ የሕክምና ባለሙያዎች ይህንን የሚከለከል ሕግ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በምዕራቡ ዓለም የነበረው ልማድ የቆመው የሳንባ ምች በመስፋፋቱ ነበር።

ከ19ኛው እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ድረስ የጀርም ምርምር እያደገ መምጣቱ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ስትል ጋዜጠኛ ቪዲያ ክሪሽናን ትገልጻለች።

“ጀርሞች እንዴት እንደሚስፋፉ መታወቁ አዳዲስ ማኅበራዊ ልማዶችን ፈጠረ። ሰዎች ማስነጠስና ማሳልን ስለመከላከል እና ስለመጨባበጥና መሳሳም ተምረዋል። የቤት ውስጥ ንጽህና አጠባበቅ ግንዛቤ ወደ አደባባይም ወጥቷል።”

ክሪሽናን እንዳለችው የግንዛቤ መጨመር በወንዶች ላይ “የባህሪ ለውጥ” እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ወንዶች ምራቅ እየተፉ እንደ ቲቢ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እንዲስፋፉ አድርገው ነበር።

እንደክሪሽና ከሆነ ሕንድ ምራቅን ለማሸነፍ በርካታ መሰናክሎች ከፊቷ አሉ።

ግዛቶቿ ይህን ልማድ ለማስወገድ ብዙ ጥረት አድርገው አያውቁም።

ምራቅ መትፋት አሁንም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አለው።

ትምባሆ እያኘኩ፣ ስፖርተኞች በካሜራ ፊት ሆነው ወይም የቦሊውድ ተዋንያን እርስ በርስ ሲጣሉ መትፋት የተለመደ ነው።

ናራሲምሃን በዘመናዊ የምራቅ መትፊያ እቃ እጦት ያዝናል።

“መትፋት ቢኖርብኝስ የት ነው የምተፋው? ልጅ ሳለሁ ከልካታ ውስጥ በአሸዋ ተሞልተው በመብራት አንጨቶች ላይ የታሰሩ የምራቅ መትፊያ እቃዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ያ በመጥፋቱ ሰዎች በየቦታው ይተፋሉ” ይላል።

ከዚህም የሚበልጡ ፈተናዎች አሉ።

ክሪሽና “መጠነ ሰፊ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ የተለያየ ዘርን፣ የኅብረሰብ ደረጃን እና ጾታን ማካተት ያስፈልጋል” ትላለች።

የጤና ባለሙያዎች ሰዎችን ለምን እንደሚተፉ ለመረዳት ሳይሞከር መቅጣት ብቻ ከልማዱ ጋር የሚደረገውን ጦርነት እንደማስቆም አስጠንቅቀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ ሁለት ዓመት ቢቆጠርም ይህን ልማድ ለመቅረፍ ያለው ተስፋ እየቀነሰ ነው።

ራጃ እና ፕሪቲ ናራሲምሃን በጎዳና ላይ በሚያደርጉት ውጊያ ግን ተስፋ አልቆረጡም።

ብዙ ሰዎች መትፋት ለኮቪድ-19 መስፋፋት አስተዋጽኦ እንዳለው አያውቁም ይላሉ።

“ጊዜን እያባከንን ከሆነም ይሁን። መሞከር እንቀጥላለን። ሁለት በመቶ ሰዎች ላይ እንኳን የአመለካከት ለውጥ መፍጠር ከቻልን ለውጥ አምጥተናል ማለት ነው” ይላል።