15 የካቲት 2022, 08:23 EAT

አባ ኪያሪ

በናይጄሪያ እውቅ የሆነው የፖሊስ መኮንን የዓለም አቀፍ አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ አባል ነው በሚል የቀረበበትን ክስ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

አባ ኪያሪ የተባለው ፖሊስ ከዚህ ቀደም ሁሽፐፒ የተባለው የኢንስታግራም አጭበርባሪ ገንዘቡን አሜሪካ ውስጥ እንዲያዘዋውር ረድቷል በሚል በቀረበበት ክስ ከሥራው የታገደ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከኮኬይን እፅ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦበታል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ኪያሪ ከፍተኛ መጠን ያለውን ኮኬይን እንዲያዘዋውር እንዲረዳው የሥራ ባልደረባውን ጠይቋል።

ለዚህም ከ61 ሺህ 400 ዶላር በላይ ጥሬ ገንዘብ ለባልደረባው ሲሰጠው በካሜራ ተይዟል ብለዋል።

የፖሊስ መኮንኑ በቀረበበት ክስ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ኪያሪ በቁጥጥር ሥር የዋለው የናይጄሪያ ብሔራዊ የአደንዛዥ እፅ ሕግ ማስከበር ኤጀንሲ “በወንጀል ተፈላጊ” መሆኑን ካሳወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።

“የብራዚል- ኢትዮጵያ- ናይጄሪያ ሕገ ወጥ አደንዛዥ እፅ ዝውውር ሰንሰለትን የሚያንቀሳቅስ የአደንዛዥ እፅ አቅራቢ ቡድን አባል” ሲልም ክስ አቅርቦበታል።

ከፍተኛ ምርመራ ከተደረገ በኋላም ኪያሪ ሰኞ ዕለት ሰንደይ ኡቡሃ፣ ባዋ ጀምስ ፣ ሳይመን አግሪግባ እና ጆን ኑሁ ከተባሉ አራት ሌሎች የፖሊስ መኮንኖች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም ጆን ኡሞሩ የተባለ ሌላ የፖሊስ መኮንንም በቁጥጥር ሥር እንደቆየ ገልጿል።

ምርመራውን ተከትሎ በደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ኡኑጉ ከተማ ያሉ በርካታ የፀረ አደንዛዥ እፅ መኮንኖች ኪያሪ ይሰራበታል ተብሎ በተከሰሰበት ቡድን የክፍያ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው መገኘቱን የናይጄሪያ ፖሊስ አስታውቋል።

የ46 ዓመቱ ኪያሪ ከፍተኛ የወንጀል ድርጊቶች ላይ በሚያደርገው ምርመራ ‘ምርጥ ፖሊስ’ የሚል ስም ነበረው።

እአአ በ2016 እርሱ የሚመራው የፖሊስ ቡድን በሌጎስ ሦስት የታገቱ ተማሪዎችን ማስለቀቁን ተከትሎ ከፕሬዚደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶለታል።

እአአ በ2011 እና በ2013 መካከል ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታትም ለጀግንነት የሚሰጠውን ከፍተኛ ሽልማት በማሸነፍ በሌጎስ መንግሥት ክብር ተሰጥቶታል። ከፖለቲከኞችና ከታዋቂ ሰዎች ጋርም በወዳጅነት ይታወቃል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የናይጄሪያ ፖሊስ አባላት የኢንስታግራም ታዋቂ ግለሰብ ሁሽፑፒ በትክክለኛ ስሙ ራሞስ አባስ ለተባለ ግለሰብ ክፍያ አመቻችቷል በሚል አሜሪካ ክስ ካቀረበች በኋላ ከሥራው ታግዶ ነበር።

በኢንስታግራም 2.4 ተከታዮች ያሉት ሁሽፐፒ ባለፈው ዓመት ከዱባይ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ በአሜሪካ ውስጥ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።