16 የካቲት 2022, 10:34 EAT

የሕዝብ ተወካዮች ምክርት ቤት ትናንት በመላ አገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ማጽደቁን ተከትሎ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች እንዲፈቱ ተጠየቀ።
በአዋጁ ምክንያት የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ከጠየቁት መካከል የአሜሪካ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይገኙበታል።
የአሜሪካ መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዙ አዋጅ እንዲነሳ መወሰኑን በመልካም ጎኑ እንደሚቀበለው ገልጾ፤ እየቀጠለ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደ አንድ አዎንታዊ እርምጃ ነው ብሎታል።
በተለይ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በሰፊው ሲዘገብ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ ህወሓት እና አጋሮቹ የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የደቀኑትን አደጋን ለመከላከል እንዲያስችል በሚል ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
ይሁን እንጂ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ያለውን ስጋት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ተግባር መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ነው ብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን ውሳኔ አጽድቋል።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በመግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደመነሳቱ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉ እና ክስ ያልተመሰረተባቸው ሰዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠይቋል።
የአሜሪካ መንግሥት የእነዚህ እስረኞች መፈታት ሁሉን አካታች እና ውጤታማ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ያስችላል ብሏል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ የተወካዮች ምክር ቤት ማፅደቁን ተከትሎ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ አዋጁ እንዲነሳ መወሰኑን በበጎ ጎኑ ተቀብየዋለሁ ያለው ኮሚሽኑ፤ ከአዋጁ አተገባበር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር የዋሉ እና አሁንም ያልተለቀቁ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው የተለቀቁ ሰዎችም በእስር ስለመቆየታቸው ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ገልጿል።
ስለሆነም ኮሚሽኑ ሰዎች በእስር የቆዩበትን ጊዜ ማስረጃና ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች የመስጠቱን ሂደት እንዲፋጠን ኢሰመኮ ጠይቋል