

16 February 2022
ከቻይናው ዌስት ኢንተርናሽል ኩባንያ ጋር አጋርነት መሥርቶ ከወራት በፊት በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እንሳሮ ወረዳ፣ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ለመገንባት በሥራ ላይ የሚገኘው ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ ኩባንያ፣ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙበትን የድንጋይ ከሰል የመተካት አቅም ያለውን ተክል፣ ወደ ኃይል ምንጭነት የመቀየር ፕሮጀክትን ዕውን ሊያደርግ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
የአክሲዮን ኩባንያው አንድ አካል የሆነው የኢስት አፍሪካ ማይኒንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ሃምዛ ለሪፖርተር እንደተናጋሩት፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች በስፋት የሚገኘውንና በሳይንሳዊ ስሙ ፕሮሶፒስ በተለምዶ ‹‹የወያኔ ዛፍ›› የሚባለውን ተክል፣ ወደ ኃይል ምንጭነት ለመቀየር ላለፉት ስምንት ዓመታት ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ከአዋጭነት ባሻገር የተክል ዝርያው ለኃይል ምንጭነት ተስማሚነቱ እንደ ኬንያ፣ ናሚቢያና አሜሪካ ባሉ አገሮች ናሙናዎች ተልከው የኃይል ምንጭ አቅም መጠኑ ተፈትሿል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1.5 ሚሊዮን ሔክታር በላይ በተለምዶ ክፉ ዛፍ (Evil Tree)፣ በሌላ አጠራሩም የወያኔ ዛፍ ሽፋን እንዳለ በጥናት ተረጋግጧል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ይህንን አማራጭ ቢጠቀሙ ለመጪዎቹ 50 ዓመት እንደሚያገለግላቸው በጥናት ተረጋግጧል፡፡about:blank
በሁለቱም ክልሎች የማኅበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖው የተመለከቱ ጥናቶች እንደተሠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በሻገር ከሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተደደሮች አንስቶ እስከ ቀበሌ ድረስ ካሉ አስተዳደር አካላት ጋር በተደረገው ውይይት የዕፅዋት ዓይነቱ ካለው ጉዳት አንፃር ቢወገድላቸው እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት ደረጃ በግብርና ሚኒስቴር ሴክሬታሪያትነት የሚመራ በተክሉ የሳይንሳዊ ስያሜ የሚጠራ የብሔራዊ ፕሮሶፒስ ማኔጅመንት ካውንስል እንደተቋቋመ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ፣ ፕሮጀክቱን የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ኢንስቲትዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ደግሞ የኢስት አፍሪካ ማይኒንግ ኮርፖሬሽን ባለሙያ የቴክኒክ ኮሚቴው አባል ናቸው፡፡
የኮርፖሬሽኑ አካል የሆነው ናሽናል ሲሚንቶ ተክሉን ለኃይል ምንጭነት የመጠቀም ሐሳብ ከማመንጨት አንስቶ በርካታ ጥረቶችን በማድረጉ የፕሮጀክቱ ሙከራ በፋብሪካው እንዲሆን ከስምምነት እንደተደረሰ የተገለጸ ሲሆን፣ የፕሮጀክት ሐሳቡ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከሚመጣው ወርልድ ክላይሜት ፈንድ ድጋፍ እንዲያገኝ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
አቶ ገዛኸኝ እንዳስታወቁት ለማሽኑ የሚሆነው አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ውድ ሲሆን፣ ለአብነትም ሁለት የማጨጃና አንድ የሥር መንቀያ ማሽን ከእነ ተጓዳኝ ዕቃዎቹ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መንግሥት ከወርልድ ክላይሜት ፈንድ 200 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡ ይህ ሥራ መንግሥትንም ሆነ የሲሚንቶ አምራች ዘርፉን የሚጠቅም እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የግል ዘርፉ ለምርት ግብዓትነት አማራጭ ሲያገኝ በሌላ በኩል መንግሥት ከተክል ዝርያው ነፃ የሆነውን መሬት አንድም ለግጦሽ፣ እንዲሁም ለቆላ እርሻ ፕሮጀክት ሊተገበርበት ይችላል፡፡ ማሸኖቹ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኩል ከጀርመን ተገዝተው ከጂቡቲ ወደ ሰመራ ደረቅ ወደብ እየተጓጓዙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በናሽናል ሲሚንቶ በኩል አማራጩን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሆነ ተገልጾ ይህም ከውጭ የሚገዙ ማሽኖች፣ የተክል ዝርያው ከታጨደ በኋላ በትራንስፖርት ተጓጉዞ ወደ ፋብሪካው ጭኖ በመውሰድ የሚከናወነውን ሥራ የሚያጠቃልል ነው፡፡
በቅርቡ በሁለቱ ክልሎች አጨዳ እንደሚጀመር የተነገረ ሲሆን፣ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለመቀየር በዚህ ወቅት ባለው ምንዛሪ ሲሰላ 30 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ያወጣል ተብሏል፡፡
የማጨጃ ማሽኑ አጭዶ ፈጭቶ የሚገኘው ዱቄት መሰል ግብዓት ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካው ገብቶ በማሽኑ እየተስተካከለ እንዲቃጠል ተደርጎ፣ ለኃይል ምንጭነት እንዲውል እንደሚደረግ አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡
ይህ አማራጭ ዕውን መሆኑ አንደኛ ከውጭ ለድንጋይ ከሰል በሚል የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያድን ሲሆን፣ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች አማካኝነት የሚደርሰውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት የሚቀንስ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ድርጅቱ ድሬዳዋ በሚገኘው የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ፕሮጀክቱን ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ ከአምስት ዓመት በፊት ዳውሮ ላይ የተቋቋመ የከሰል የማዕድን ማውጫ ቦታ እንደነበረው የተገለጸ ሲሆን፣ አገሪቱ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ያለመረጋጋት ምክንያት ሥራ አቁሞ ነበር፡፡ ዳግም በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ድርጅቱ ከማዕድን ሚኒስቴር የከፍተኛ ምርት የማምረት ፈቃድ ወስዷል፡፡ ከባዮ ማሱ ፕሮጀክቱ ጎን ለጎን ማዕድን ሚኒስቴር በዘረጋው ስትራቴጂ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የድንጋይ ከሰል ምርቶች ታጥበው ደረጃቸው ከፍ እንዲል የማድረግ ሥራ እንዲከናወን የተሰጠውን ፈቃድ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የሽርክና አጋሩ ከሆነው የቻይናው ዌስት ኢንተርናሽል ሆልዲንግ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመሥራት ከስምምነት እንደተደረሰ ተገልጿል፡፡
በዳውሮ ዞን የሚተከለው የድንጋይ ከሰል እጥበት ማሽን ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ፣ እንዲሁም መሰል ከሰል አምራቾች የሚያመርቱትን ምርት በማጠብ ለፋብሪካ ግብዓትነት እንዲያገለግል ይደረጋል፡፡ በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ሥር በግንባታና በሥራ ላይ ያሉት ፋብሪካዎች በወር 70,000 ሺሕ ቶን የሚደርስ ከሰል ያስፈልጋቸዋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ከሚያስችለው ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው የባዮ ማስ ኃይልና ሁለተኛው ደግሞ በበቂ መጠን የተመረተ የድንጋይ ከሰል ነው፡፡
የድንጋይ ከሰል እጥበት ፕሮጀክት ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ 200 ሚሊዮን የሚደርስ ወጪ እንደሚጠይቅ፣ ይህንን ፕሮጀክት ድርጅቱ በተናጠል ብቻውን የሚተገብረው ሳይሆን ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የታቀዱ ተግባራትን ከሚመለከተው የክልሉ መንግሥት አካላት በሚደረግ ንግግሮች መሠረት ተድርጎ ተግባራዊ እንደሚደረግ፣ ማሽኑም ከቻይና ኩባንያ የሚደረገውን ስምምነት እንደተጠናቀቀ በመጪዎቹ ሁለትና ሦስት ወራት ወደ ተግባር እንደሚገባ አቶ ገዛኸኝ አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘም ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከዌስት ቻይና ሊሚትድ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር ጥምረት በመፍጠር ግንባታው የተጀመረው የሲሚንቶና ተዛማጅ ግብዓቶች ግንባታ ፕሮጀክት በታቀደው ልክ እየሄደ እንደሚገኘ የተገለጸ ሲሆን፣ የጂብሰም ፋብሪካ የሚያርፍበት ቦታ ላይ ያለው የመሬት ጥርጊያና ማስተካከል ሙሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀ፣ በሌላ በኩል የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ የሚያርፍበት ቦታ ላይ የሚሠራው የመሬት ጥርጊያና ማስተካካል ሥራ 60 በመቶ መድረሱ ተገልጸ፣ ቀሪ የጥርጊያ ሥራዎች ተጠናቀው የመሥሪያ ቦታና የማሽን ተከላ ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሏል፡፡