ዜና

ፖለቲካ

16 February 2022

አማኑኤል ይልቃል

ለብዙ ጊዜያት ሲነገር ለነበረው የባንክ ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ውጥን ተግባራዊ ቢደረግ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች ለተወዳዳሪነት የሚያበቃ አቋም እንደሌላቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

መንግሥት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለድርሻዎች ክፍት የማድረግ ሐሳብን ካነሳ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ይኼንን መቋቋም የሚያስችል አቅም እንዳላዳበሩ ተገልጿል፡፡ በተለይ የሰው ኃይልን በማዳበር በኩል ያለባቸው ክፍተት የባንኮቹን አመራሮች አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ትምህርት ቤት መምህር ዳኪቶ ዓለሙ (ዶ/ር) ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ቢሆን፣ የአገር ውስጥ ባንኮች የሚኖራቸው የተወዳዳሪነት ቁመና ላይ ያተኮረ አነስተኛ ጥናት ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እንደ ዳኪቶ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ባንኮቹ ከፋይናንስ አቅም አንፃር ዓለም ላይ ያሉ መሥፈርቶችን በመጠኑም ቢሆን ማሟላት የሚያስችል ካፒታል አላቸው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ኪሳራ የማይታይበትና ከምሥረታ ጀምሮ ትርፍ የሚገኝበት መሆኑን ያክላሉ፡፡

ነገር ግን እንደ መምህሩ ገለጻ፣ ባንኮቹ ትርፋማ የሆኑት በመንግሥት ብዙ ቁጥጥርና ጥበቃ ስለሚደረግላቸውና ዓለም አቀፍ ባንኮች እንዲገቡ ስለማይፈቀድ ነው፡፡ ‹‹ባንኮቹ በንግድ ዕይታቸው ደካማ፣ ጥበቃ ስለተደረገላቸው ግን ትርፋማ ነው የሆኑት፤›› ያሉት ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ በባንኮቹ ዘንድ የቢዝነስ አተያይና የአስተዳደር ችግር በመኖሩ ከውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር እንደማያስችላቸው ያስረዳሉ፡፡

ብዙዎቹ ባንኮች ቀላል የማይባል ገቢያቸው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በሚያስተላልፉት የውጭ ምንዛሪ ላይ የተመሠረተ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰው፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ወስጥ ከገቡ ግን የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራቸው ውጭ ካላቸው ቅርንጫፍ ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቅርንጫፍ ማስተላለፍ ስለሚሆን፣ እንደሚቀላቸውና የአገልግሎት ክፍያቸውም እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበትን አንዱን መንገድ ሊያጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ባንኮች ልምድን ያካበቱ፣ ክህሎት ያላቸውና የንግድ ሞዴላቸውን በሁሉም አገር መተግበር እንዲቻል አድርገው የሚያዘጋጁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሥራ  ለመጀመር በዝግጅት ላይ ያለው አሀዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬም በዚሁ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ በተለይ የውጭ ባንኮች ያላቸው ዓይነት የአስተዳደር ክህሎት ያለው አመራር፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ጋ አለመኖሩን እንደ ፈተና ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በፋይናንስ ባንክ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ሥልጠና የምስክር ወረቀት ያለው ሰው ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የኅብረት ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያ መሥራችና የባንክ ዘርፉ ለዓለም ገበያ ክፍት እንዲሆን በመጠየቅ የሚታወቁት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ለተወዳዳሪነት የሚያበቃ ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም አለመኖሩን በመጥቀስ፣ የሰው ኃይል ላይ ክፍተት ስለመኖሩ ይስማማሉ፡፡ ባንኮቹም ቢሆኑ ካፒታላቸውን ከማሳደግ ባሻገር የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ላይ ዕርምጃዎች እንደሚቀሯቸው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ303 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያስገነባው አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ምረቃ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የባንክ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ የማይቀር መሆኑን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር ለሚኖር ውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል፡፡

ላለፉት 30 ዓመታት ምንም ዓይነት የውጭ አገር ባንክ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ተደርጎ፣ ለአገር ውስጥ ባንኮች ከለላ እንደተሰጠ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ሁኔታ እንደማይቀጥል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ባንኮች ከዓለም ዕድገት ጋር የሚጓዝና ከሌሎች አገሮች ባንኮች ጋር ለመወዳደር የሚያበቃ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበው፣ ዝግጅቱ በሕንፃ ግንባታ ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይል ዝግጅትን፣ የአሠራር ቅልጥፍናንና ፍጥነትን ያካተተ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 80 ዓመታት ለሌሎች ባንኮች አርዓያ ሆኖ እያስተማረና እያሳደገ መምጣቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ደግሞ ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚኖረው ውድድር ራሱን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የፋይናንስ ዘርፉ ዋንኛ ተዋናዮች በተገኙበት የንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ተሸብቦና ተደብቆ የባንክ ባለቤትና ፕሬዚዳንት መሆን፣ ዘመኑ ያበቃ መሆኑን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ፤›› ብለው፣ ከእንግዲህ በኋላ የባንክ ቅርንጫፎችን ብዛት መናገር ለባንክ ዕድገት መመዘኛ መሆን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ሲባል ባንኮች ራሳቸውን በሚገባ አዘጋጅተው ለሰፊ የፋይናንስ ሩጫና ትግል እንዲያበቁ አሳስበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን ከኢትዮጵያ በማሻገር ቀጣናዊና አኅጉራዊ ህልውና ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ግን የኢትዮጵያ ባንኮች ከአገር ያለፈ አገልግሎት ለመስጠት ያላቸው አቅም ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ ከውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር ያላቸው ዝግጁነት ላይ ጥርጣሬ አላቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የራሳቸውን ዕውቀት ተጠቅመው ባንኮችን እንዲያደራጁና እንዲያስተዳድሩ ብዙ ጥረት ቢደረግም ውጤታማ አለመሆኑን የተናገሩት ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኘው አሀዱ ባንክ ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ፣ ብሔራዊ ባንክ ዘርፉን ለዓለም ክፍት ከማድረጉ አስቀድሞ ሌሎች አገሮች የደረሱበት ዓይነት የባንክ ክህሎትና ዕውቀት ያላቸው ሰዎችን መፍጠር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በ1940ዎቹ የመንግሥት ባንክ ወደ ብሔራዊና ንግድ ባንክ ከመከፈሉ በፊት 500 ያህል ሰዎች ወደ ህንድ፣ ማሌዥያ፣ አሜሪካና ካናዳ ሄደው ስለባንክ ዘርፍ ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉን የጠቀሱት የአሀዱ ባንክ ፕሬዚዳንት፣ አሁንም ብሔራዊ ባንክ ከአገሮች ጋር በመነጋገር ከአንድ ሺሕ ያላነሱ ሰዎች ለሥልጠና ወደ ውጭ እንዲሄዱ ማድረግ አለበት የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ድረስ የማስገደድ አቅሙን ነው በሥራ ላይ እያዋለ ያለው፣ የማትጋት አቅሙን ተጠቅሞበት አያውቅም፤›› የሚሉት አቶ እሸቱ፣ ባንኮች የተለያዩ ብድሮችን ማቅረብ የሚያስችላቸውን የዕገዛ ሥራ ማከናወን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት የካፒታል ገበያን በታሰበው መንገድ ሳያሳልጥ የባንክ ዘርፉን ለመክፈት የሚሞክር ከሆነ፣ የባንኮች ሀብት በቅጡ ሳይታወቅ ድርሻቸው በቅናሽ ዋጋ እንዲሸጥ ሊያደርግ እንደሚችል ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡

ዳኬቶ (ዶ/ር) በተቃራኒው ብሔራዊ ባንክ ላለፉት ስምንትና አሥር ዓመታት ባንኮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጊዜ መስጠቱን በመጥቀስ፣ በጉዳዩ ላይ ይበልጥ መጨነቅና ማሰብ ያለባቸው ዘርፉ ላይ ያሉ የአገር ውስጥ ባንኮችና አስተዳደሮቻቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ዘርፉን ለዓለም ክፍት እንዲያደርግ የሚያስገድዱት ጫናዎች እንዳሉ የሚያስረዱት የፋይናንስ መምህሩ፣ ‹‹ጉዳዩ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ቅድመ ሁኔታ ነው፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ገንዘብ ለማግኘትም በመሥፈርትነት የሚነሳበት ሁኔታ አለ፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ባንኮች ተወዳዳሪነታቸውን ለመጨመር ውህደትን እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ እንዳለባቸው የጠቆሙት ዳኬቶ (ዶ/ር)፣ ይሁንና የአገር ውስጥ ባንኮች ካላቸው ውስጣዊ ‹‹አስቸጋሪ ፖለቲካ›› ጋር በተያያዘ መዋሀድ ላይ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ባንኮቹ ፖለቲካዊ ንክኪ ያላቸው ወይም ብሔርን አልያም ሃይማኖትን መሠረት አድረገው የተመሠረቱ በመሆናቸው፣ ለውህደቱ እንደ አንድ ችግር አንስተዋል፡፡ መንግሥት እንደሚያስቀምጠው የሚወሰን ቢሆንም፣ ከውጭ ከሚመጡ ባንኮች ጋር መጣመርም አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዳኬቶ (ዶ/ር) ምልከታ ባንኮቹ አቅደው ከሠሩ፣ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መሆኑ ምናልባትም የተሻለ ዕድል ሊያመጣላቸው ይችላል፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው መንግሥት የባንክ ዘርፉን ለዓለም ክፍት የማድረግ ሒደቱን በታቀደ፣ የተለያዩ ደረጃዎች ባሉትና በተናበበ መንገድ ማስኬድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ለመጀመሪያ ያህል የውጭ ባለሀብቶች የኢትዮጵያን ባንኮች የተወሰነ ድርሻ እንዲገዙ በማድረግ፣ የሚፈለገውን ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትና የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ አንስቶ፣ ለብዙ ጊዜያት ሲነገር በቆየው የተለያዩ ዘርፎችን ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሥራ ላይ ተጨባጭ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ ከ120 ዓመታት በላይ በአገር ውስጥ ኩባንያ በብቸኝነት ተይዞ የቆየውን የቴሌኮም ዘርፍ ክፍት በማድረጉም፣ የኬንያው ሳፋሪኮም ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ሆኖ ሊጀምር ጫፍ ደርሷል፡፡

የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት የባንኩ ዘርፍ ላይም ተመሳሳይ ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወሰድ ሲገለጽ የነበረ ቢሆንም፣ ዕቅዱ ከዚህ አስቀድሞም ሲነሳ የነበረ ነው፡፡ በ1986 ዓ.ም. የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በባንክ ዘርፍ እንዲሰማሩ የፈቀደው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ የባንክ ዘርፉን በ2014 ዓ.ም. ላይ በከፊል ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ግብ አስቀምጦ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ለውጥ እንዲያደርግ ያስገደደው ተቃውሞ በኢትዮጵያ አለመረጋጋትን በመፍጠሩ፣ ይህንን ዕቅዱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ መተግበር እንዳልቻለ ይታወቃል፡፡

ይሁንና አሁን ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀው የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሥራ፣ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በ1956 ዓ.ም. ተመሥርቶ የነበረው የአዲስ አበባ ባንክ 40 በመቶ ድርሻው በእንግሊዝ ናሽናል ኤንድ ግሪንድሌይ ባንክ (National and Grindlay Bank) የተያዘ ነበር፡፡