

16 February 2022
የአሜሪካ መንግሥት የልማትና ተራድኦ ድርጅት (USAID)፣ በኢትዮጵያ ደቡባዊና ደቡብ ምሥራቃዊ አካባቢዎች በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት የሚውል ከ39 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ሰብዓዊ ዕርዳታ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የዩኤስኤአይዲ አጋር በሆነው የዓለም የምግብ መርሐ ግብር አማካይነት ድርቅ ላጋጠማቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ይቀርባል የተባለው ዕርዳታ፣ 1.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ በድርቅ የተጎዱ ሰዎችና ስደተኞች የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ድጋፉ የትምህርት ቤት ምገባን፣ እንዲሁም ለሕፃናት፣ ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እናቶች የምግብ አቅርቦትን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡
የአሁኑ የዩኤስኤአይዲ የ39 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ድርጅቱ በድርቅ ለተጎዱ 3.4 ሚሊዮን ሰዎችና አስቸኳይ ምገባ ለሚያስፈልጋቸው 300 ሺሕ ሕፃናት እያደረገ ካለው ድጋፍ ተጨማሪ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዩኤስኤአይዲ ይኼንን ዕርዳታ እንደሚያደርግ ያስታወቀው፣ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሻን ጆንስ ባለፈው ሳምንት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ድርቅ ያለባቸውን አካባቢዎች ከጎበኙ በኋላ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ በሶማሌ ክልል ጉብኝታቸው ወቅት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ጋር እንደተወያዩ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ባደረጉት ጉብኝት በድርቁ የተጎዱ አርብቶ አደሮችን መመልከታቸው ተገልጿል፡፡
እንደ ድርጅቱ መረጃ በሁለቱ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2022፣ 6.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የድርቁ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ደቡባዊና ደቡብ ምሥራቃዊ አካባቢዎች በግልጽ እየታየ መሆኑን የገለጸው ዩኤስኤአይዲ የግጦሽ መሬቶችን መቀነስ፣ ከፍተኛ የሰብል መጥፋት፣ የውኃ እጥረትና የእንስሳት ሞት መኖሩን አስታውቋል፡፡
አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2021 የበጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በመላ አገሪቱ በግጭት፣ ድርቅና ሌሎች ቀውሶች ለተከሰቱት ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሰጠች፣ በተመሳሳይም ዩኤስኤአይዲ በ2021 ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ዕርዳታ ለድርቅ ምላሽ ማቅረቡ ተገልጿል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ አገሮች ውስጥ የተከሰተው ድርቅ 13 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎችን ለከፋ ረሃብ ያጋልጣቸዋል የሚል ሥጋቱን ገልጾ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ የተወሰኑ ክፍሎች ለሦስት ተከታታይ ወቅቶች ባለመዝነቡ የተነሳ የተከሰተው ድርቅ ከ30 ዓመታት ወዲህ ያጋጠመ ትልቁ ድርቅ ነው ብሏል፡፡
በዚህም ምክንያት ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ አርብቶ አደሮች እንስሳቶቻቸውን እያጡ ነው፡፡ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች እያንዳንዳቸው ከ200 ሺሕ በላይ እንስሳት በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዓለም ፕሮግራም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ አስቸኳይ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 4.5 ሚሊዮን ሰዎች ለመድረስ፣ 327 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡