አሜሪካ በኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዙ አዋጅ እንዲነሳ መወሰኑን በመልካም ጎኑ እንደምትቀበል ገልፃለች።
ውሳኔው እየቀጠለ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደ አንድ አዎንታዊ እና በጎ እርምጃ ነው ብላዋለች።
አሜሪካ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቷ ባወጣችው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደመነሳቱ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉ እና ክስ ያልተመሰረተባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቃለች።
የእስረኞች መፈታት ሁሉን አካታችና ውጤታማ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ያስችላልም ብላለች።
አሜሪካ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ፣ ያልተቋረጠ የሰብአዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ፣ በሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች ላይ ግልፅ ምርመራዎች እንዲደረጉ እና ግጭቱን በድርድር እንዲፈታ ከሁሉም አካላት ጋር መነጋገሯንና መጣሯን እንደምትቀጥል ገልፃለች።
” ውሳኔውን በጣም ነው የምናደንቀው ” – ተመድ
የተባበሩት መግሥታት ድርጅት (UN) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን በጣም እንደሚያደንቀው አሳውቋል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪች ፤ ትላንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትና የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ስላላቸው አቋም ተጠይቀው ድርጅቱ ውሳኔውን ” በጣም እንደሚያደንቀው ” ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የተያዙ እና የታሠሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ፣ አሁንም ግጭት መቆም እንዳለበት ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና ተደራሽነት እንዲሁም ደግሞ ተጠያቂነት መስፈን እንዳለበት ቃል አቀባዩ አንስተዋል።
” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ ነው ” – ቱርክ
ቱርክ የኢትዮጵያ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መወሰኑን በበጎ እንደምትቀበል ገልፃለች።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ትክክለኛ እርምጃ ነው ስትልም ገልፃለች።
በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚደረጉ ሁሉንም ጥረቶች መደገፏን እንደምትቀጥል የገለፀችው ቱርክ ለስኬታማነቱም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እሰራለሁ ብላለች።