በማይካድራ ከተማ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ከተፈጸመ ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰሱ የ202 ተከሳሾች ክስ፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰማ።
በተክዩ በሪሁ የክስ መዝገብ የተካተቱ አጠቃላይ 202 ተከሳሾች ሲሆኑ 80 ተከሳሾች ያልተያዙ ናቸው።
ያልተያዙት ተከሳሾች በማይካድራ ከተማ በአድራሻቸው አለመገኘታቸውን ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ፖሊስ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
ነገር ግን ቀሪዎቹ መምህር ጃንቦ ብርሀነ፣ ገ/መድህን አብርሃ፣ ኪሮስ ሲሳይ፣ ሀፍቶ ካሳይ፣ አለምፀሀይ አሰፋን ጨምሮ 22 ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ቀርበው በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ ችሎቱ የተሰየመው ተከሳሾች አማንኤል ሊቃኖስ የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግለት የተሰጠውን ትዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ እና ክሱን በንባብ ለማሰማት ሲሆን ለተከሳሹ ጥሪው መደረጉን ችሎቱ አረጋግጧል።
ሆኖም ዛሬ ተደጋጋሚ ጥሪው የተደረገላቸው ተከሳሽ አማኑኤል ችሎት ያልቀረበ መሆኑን ተከትሎ ከሳሽ ዓቃቢህግ በሌሉበት ጉዳዩ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ትዛዝ በመስጠት የተከሳሾችን ክስ በችሎት በንባብ አሰምቷል።
በዚህ ክስ ላይ ከ1ኛ እስከ 15 ያሉ ተከሳሾች ከጥቅምት 14 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 በማይካድራ ከተማ በተለያዩ ቀበሌና ቀጠናዎች የአማራ መሬታችሁን ሊቀማ እየመጣ ነው ጠንክራችሁ ተዋጉ ግደሏቸው በማለት፤ የትግራይ ብሔር ተወላጆችን በማደራጀት፣ ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ በማልበስ ገጀራ፣ መጥረቢያ፣ ካራ የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ በመምራት በማነሳሳት በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1ሀናለ 35:38 እና አንቀጽ 240 /2 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ የተከሰሱ መሆኑ በንባብ ተሰምቷል።
በ2ኛ ክስ ደግሞ ከ16 ኛ ዕስከ 202 ኛ ተራ.ቁ ባሉ ተከሳሾች በየደረጃው በራሳቸው ፍቃድ ተሳታፊ በመሆን በገጀራ፣ በካራ፣ በዱላ ከ 219 በላይ የአማራ ተወላጆችን በመታወቂያና በቤት በመለየት በተለያዩ የሰውነት ክፍላቸው ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ምላስ በመቁረጥ፣ ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግ፣ አስከሬናቸውን በጊሊደር ጭኖ በመውሰድና በጅምላ በመቅበር ተሳትፏቸው በችሎቱ ተነቧል።
በተጨማሪም ከ217 በላይ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የአካል ጉዳት በማድረስ በ10 ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት በመፈጸም እንዲሁም የ 17 ሚሊዮን 620 ሺህ ብር ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም በማድረግ በተነሳ የዕርስ በዕርስ ጦርነት በመሳተፍ በመንግስት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ተከሰዋል።
አጠቃላይ ተከሳሾች በተሳትፏ ደረጃቸው ዓቃቢህግ 44 ክስ ነው ያቀረበባቸው።
ክሱ ከተነበበ በኋላ የተከሳሽ ጠበቆች ሀብቶም ተከስተ እና ዘራይ ወ/ሰንበት በተነበበው ክስ ላይ የክስ መቃወሚያ እያዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ቀጠሮ እንደሚያቀርቡ ማብራራታቸውን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።
ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ውጤት ለመጠባበቅ ለየካቲት 21 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።