17 የካቲት 2022

አሜሪካዊቷ ታካሚ በታሪክ ከኤችአይቪ ነፃ የሆነች የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።
ታካሚዋ ሉኪሚያ ለተሰኘው በሽታ እንዲሆን በማለት ከሌላ ሰው የስቴም ሴል ተለግሶላት ነው ከኤችኤይቪ የዳነችው።
ኤድስን የሚያስከትለው ኤችአይቪ ቫይረስን በመቋቋም የሚታወቀው ስቴም ሴል የተሰጣት ግለሰብ አሁን ከቫይረሱ ነፃ ከሆነች 14 ቀናት ተቆጥረዋል።
ግለሰቧ ከኤችይቪ የተፈወሰች ሶስተኛዋ ሰው ስትሆን የመጀመሪያዋ ሴት ናት።
ነገር ግን የዘርፉ ሙያተኞች ንቅለ ተከላው የሚካሄደበት መንገድ ኤችአይቪ ላለባቸው ሰዎች አስጊ ነው ይላሉ።
- የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆሙ ተገለጸ
- ቴሌግራም ላይ በተጋሩ ፎቶዎች ምክንያት ሕይወታቸው የተመሳቀለ ሴቶች
- በዩክሬን ጦርነት እንዳይከሰት ያስችላሉ የተባሉ አምስት መንገዶች
የግለሰቧ የንቅለ ተከላ ሂደት ዴንቨር በተካሄደ ‘ሜዲካል ኮንፍረንስ’ ላይ ይፋ የተደረገ ሲሆን እንዲህ ዓይነት መላ ተጠቅሞ ኤችአይቪን ማጥፋት የተቻለው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሉኬሚያ የተሰኘው የካንሰር ዓይነት ያለባት ግለሰቧ ለዚህ ሕክምና እንዲሆናት በማለት ‘አምብሊካል ኮርድ’ ደም ንቅለ ተከላ ተደርጎላታል።
ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ ለኤችአይቪ የሚያስፈልጋትን ሕክምና መውሰድ አቁማለች።
አሜሪካ ውስጥ አንድ ጥናት እየተደረገ ሲሆን ኤችአይቪ ደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች የደም ንቅለ ተከላ ቢደረግላቸው ምን ይሆናሉ የሚለውን ይመለከታል።
ከሰው ተወስደው ታካሚዎች ላይ የሚገጠሙት የደም ሴሎች የመከላከል ኃይላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ከኤችአይቪ አይጠቁም።
ሳይንቲስቶች አንደሚያምኑት በዚህ ምክንያት ደሙን የሚቀበሉት ሰዎች ኤችይአቪን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅም ይኖራቸዋል።
የዓለም አቀፉ ኤይድስ ሶሳይቲ ፕሬዝደንት ሻሮን ሌዊን ይህ የደም ንቅለ ተከላ ኤችአይቪ ላለባቸው ሰዎች የሚመከር አይደለም ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።
ነገር ግን ኤችአይቪ ሊፈወስ እንደሚችል ማወቁ ትልቅ ዜና መሆኑን ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት 37 ሚሊዮን ሰዎች ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር ይኖራሉ። አብዛኛዎቹ ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት የሚኖሩ ናቸው።
በስቴም ሴል ንቅለ ተከላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኤችአይቪ የተፈወሰው ቲሞቲ ሬይ ብራውን የተሰኘው ግለሰብ ሲሆን ጊዜው ደገሞ በፈረንጆቹ 2007 ነበር።
ከዚያ በኋላ አንድ አዳም ካስቲሌዮ የተባለ ግለሰብ እንዲሁም አንድ የኒው ዮርክ ነዋሪ በተመሳሳይ በደም ንቅለ ተከላ ከኤችአይቪ ተፈውሰዋል።
ሶስቱም ታካሚዎች ካንሰር የነበረባቸው ሲሆን የደም ንቅለ ተከላው ያስፈለጋቸው ይህንን ለማከም እንጂ ኤችአይቪን ለማጥፋት አልነበረም።