17 የካቲት 2022

ቴሌግራም በተሰኘው መተግበሪያ አማካይነት የበርካታ ሴቶች እርቃን ፎቶዎች እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ በሚባል ደረጃ ሴቶቹን ለማስፈራራት፣ ለማዋረድ እንዲሁም ለማንኳሰስ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ አረጋግጧል።

ሳራ የተነሳቻቸው የእርቃን ፎቶዎች በቴሌግራም አማካይነት ለበርካታ ሰዎች እንዲደርሱ ሲደረግ ሕይወቷ በሰከንዶች ውስጥ ነበር የተመሰቃቀለው።
ከእርቃን ፎቶዎቹ በተጨማሪ የኢንስታግራም እና የፌስቡክ አድራሻዋም ተቀምጧል። ይባስ ብሎ ደግሞ የግል ስልክ ቁጥሯም ለሁሉም ሰው ይፋ ተደርጓል። በድንገት በርካታ ሰዎች የእርቃን ፎቶዎች ላኪልን እያሉ ስልክ መደወል ጀመሩ።
“ልክ የወሲብ ንግድ ውስጥ የገባሁ እንዲመስለኝ ነው ያደረጉት፤ ምክንያቱም እኔ እራሴ ፎቶዎቹን ለሰዎች ያጋራሁ ነው የመሰላቸው። እንደ ሴት ምንም ዋጋ እንደሌለኝ ነው የሆነው።”
ፎቶዎቹ በይፋ ለሰዎች ከተለቀቁ በኋላ ሳራ ከቤቷ መውጣት አቁማለች።

ሳራ ትክክለኛ ስሟ አይደለም። በወቅቱ ሳራ የእርቃን ፎቶዋን ለአንድ ለምታምነው ግለሰብ ትልካለች። ነገር ግን ወዲያውኑ እነዚህ ፎቶዎች 18 ሺህ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ቡድን ውስጥ እንዲለቀቅ ተደረገ። አብዛኞቹ የዚህ ግሩፕ አባላት ደግሞ በኩባ ሀቫና በምትገኘው መንደሯ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።
አሁን ላይ ሁሉም ሰው እርቃኗን የተመለከታት ይመስላታል። “በጭራሽ ወደ ውጪ መውጣት አልፈልግም። ከጓደኞቼም ጋር ቢሆን መገናኘት አልፈልግም። በእውነት በጣም ተሰቃይቻለው” ትላለች።
ሳራ በዚህ መልኩ ሕይወቷ የተመሰቃቀለባት ብቸኛዋ ሴት አይደለችም። ቢቢሲ ቴሌግራም ላይ ለወራት ባደረገው ምርመራ በሺዎች የሚቆጠሩ በድብቅ የተቀረጹ አልያም የተሰረቁ የሴቶች የእርቃን ፎቶተዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ቢያንስ 20 በሚደርሱ አገራት እንደሚሰራጩ ማረጋገጥ ችሏል።
ድርጅቱ ግን መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም።
- እየተለመደ የመጣው ሐሰተኛ የሴቶች የእርቃን ምስል በበይነ መረብ
- የሴቶችን የወሲብ ቪዲዮ በቴሌግራም ሲሸጥ የነበረው 40 ዓመት ተፈረደበት
- በኢትዮጵያ ፌስቡክና ቴሌግራምን ጨምሮ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አገልግሎት ተቋረጠ
ከኩባ በሺዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዘርባጃን የምትኖረው ኒጋር በዚሁ ምክንያት የትውልድ መንደሯን ለቅቃ እንድትሰደድ ተገዳለች።
በአውሮፓውያኑ 2021 ከባለቤቷ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽሙ የሚያሳይ በድብቅ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል ለቤተሰቦቿ ከተላከ በኋላ በቴሌግራም አማካይነትም ተለቋል።
“እናቴ እያለቀሰች እንዲህ አለችኝ፤ የሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል አለ። ለእኔም ተልኮልኛል። በጣም ነበር ያዘንኩት። በእጅጉ ነው የጎዳኝ።”
የኒጋር ተንቀሳቃሽ ምስል 40 ሺህ ተከታዮች ባሉት የቴሌግራም ግሩፕ ውስጥ የተለቀቀ ሲሆን በምስሉ ላይ የባለቤቷ ፊት እንዳይታይ ተደርጎ ተሸፍኗል። ነገር ግን የእርሷ ፊት በደንብ ይታያል።
ኒጋር የቀድሞ የትዳር አጋሯ በድብቅ እንደቀረጻቸው ታምናለች። ይህን ያደረገው ደግሞ የአዘርባጃን ፕሬዝዳንትን አጥብቆ የሚወቅሰው ወንድሟን ለማስፈራራት እንደሆነ ታምናለች።
“ወንድሜ ከዚህ ተግባሩ የማይመለስ ከሆነ ይህ ምስል በቴሌግራም እንደሚለቀቅ ለእናቴ ነግረዋት ነበር።”
ኒጋር እንደምትለው የቀድሞ ባለቤቷን ብታናግረውም እርሱ እንዳላደረገው ገልጾላታል። ቢቢሲም በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቀውም ፈቃደኛ አልሆነም።

ኒጋር አሁንም ወደ ቀደመው ሕይወቷ ለመመለስ በጣም ተቸግራለች። “በጣም ከባድ ነው። የአእምሮ ጤና ባለሙያ በሳምንት ሁለት ጊዜ አያለሁ። እስካሁን ምንም ለውጥ የለም። ሁሉንም ነገር መርሳት እችል እንደሆነ ይጠይቁኛል፤ መርሳት ግን አልችልም” ትላለች።
የኒጋር እና የሳራ ምስሎች ለቴሌግራም ሪፖርት ቢደረጉም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልተገኘም።
ቢቢሲ ከሩሲያ እስከ ብራዚል፣ ከኬንያ እስከ ማሌዢያ ድረስ በተከታታላቸው 18 የቴግራም ቻናሎችና 24 ቡድኖች ውስጥ ተመሳሳይ ነገሮች እንደሚፈጸሙ መረዳት ችሏል። እነዚህ ቻናሎችና ግሩፖች ደግሞ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሏቸው።
ስልክ ቁጥርና የቤተሰቦቻቸው አድራሻ ጭምር ከግርጌ ላይ የተቀመጠባቸው የእርቃን ምስሎች ጭምር በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ይለቀቃሉ። አንድ አስተዳዳሪ የቡድን አባላት የፍቅር ጓደኞቻቸውን፣ የባልደረቦቻቸውን የእርቃን ምስሎች እንዲያጋሩ ሲጠይቅም ቢቢሲ ተመልክቷል።
ቴሌግራም እንደሚለው በመላው ዓለም በአሁኑ ወቅት ያሉት ተጠቃሚዎች ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ይህ ደግሞ ከትዊተርም በላይ ነው። ሰዎች ቴሌግራምን የሚመርጡት የግል መረጃ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል ብለው ስለሚያምኑ ነው።
በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት ዋትስአፕ የግል መረጃና የደኅንነት ፖሊሲውን መቀየሩን ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቴሌግራም ፊታቸውን አዙረዋል።
ቴሌግራም በብዛት የተለመዱት መገናኛ ብዙኃን በሚታፈኑባቸው አገራት ውስጥ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው። ተጠቃሚዎች ስማቸውንና ስልክ ቁጥራቸውን ይፋ ሳያደርጉ የፈለጉትን ነገር የማጋራት አማራጭ አላቸው።
በአንድ ቡድን ውስጥም እስከ 200 ሺህ ተከታዮችን ማፍራት ይቻላል። አንዳንድ የቴሌግራም ቻናሎች ደግሞ ማንኛውም ሰው መከታተል የሚችላቸውን መረጃዎች ያሰራጫሉ።
እንደ ቤላሩስ ባሉ አገራት ፀረ መንግሥት የሆኑ መልዕክቶችን ለማስተላለፍና የተቃውሞ ሰልፎችን ለማስተባበር ቴሌግራም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ቴሌግራም እንደሚለው በማንኛውም መንገድ ተጠቃሚዎቹን መገደብ አይፈልግም። ነገር ግን አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ድርጅቱ ይህንን አሰራር መከተሉ አንዳንድ ሰዎች የእርቃን ፎቶዎችን የመሳሰሉ የግል መረጃዎችን እንዲለዋወጡበት አስችሏል።
ምንም እንኳን ቴሌግራም ለመሰል ድርጊቶች የሚሆን ቀጥተኛ ፖሊሲ ባይኖረውም በአጠቃላይ ግን ሕገወጥ ምስሎችን ማጋራት የተከለከለ መሆኑን ለተጠቃሚዎች ያሳስባል። በተጨማሪ ደግሞ የቡድኖቹ አባላት ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያገኙ ስክሪናቸውን ፎቶ በማንሳት ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ።
ቢቢሲ ይህንን የምርመራ ዘገባ በሚሰራበት ወቅት 100 የሰዎች የእርቃን ፎቶዎችን ለቴሌግራም ሪፖርት አድርጎ ነበር። ነገር ግን ከአንድ ወር በኋላ 96ቱ ፎቶዎች እርምጃ ሳይወሰድባቸው እንዳሉ ነበሩ። ቀሪዎቹ አራት ፎቶዎችም ቢሆኑ እንዲወገዱ ተደርገው ሳይሆን ቢቢሲ መግባት ከማይችልባቸው ቡድኖች ውስጥ ስለተወሰዱ ነው።
በጣም በሚያስፈራ ሁኔታ ደግሞ ሩሲያ ውስጥ ከአንድ ስኒ ቡና ባነሰ ዋጋ ህጻናት ላይ ጥቃት ሲፈጸም የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለመሸጥ የሚሞክሩም ሰዎች ነበሩ። ምንም እንኳን ቢቢሲ ጉዳዩን ለድርጅቱ ሪፖርት ቢያደርግም ከሁለት ወራት በኋላ እንኳን ቻናሎቹ እንዳሉ ነበሩ። ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ቻናሉ እንዲዘጋ ተደርጓል።
አፕል ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ቴሌግራምን ከአፕል ስቶር ሰርዞት የነበረ ሲሆን ይህንን ተከትሎም ድርጅቱ አንዳንድ ማሻሻዎችን አድርጎ ነበር። ለምሳሌም የአይሲስ ቪዲዮዎች ከቴሌግራም ሁሉም ቡድኖችና ቻናሎች እንዲጠፉ ተደርጓል።
ከግለሰቦች ግላዊ መረጃ ጋር በተያያዘ ግን ቴሌግራም የሚከተለው ፖሊሲ እምብዛም መሆኑን ተከትሎ አንዳንድ ሴቶች ጉዳዩን በራሳቸው መንገድ ለመፍታት እየጣሩ ነው።

ጆዋና ያለሰዎች ፈቃድ በቴሌግራም ቻናሎች የሚለቀቁ ምስሎችን እየተከታተለች ሪፖርት ታደርጋለች። በ13 ዓመቷ እርቃኗን ሆና የተነሳችውን ምስል በአንድ የማሌዢያ ታዋቂ ቻናል ውስጥ አግኝታዋለች። ቻናሉን የሐሰት መረጃ በማስገባት ተቀላቅላለች። በዚህም መሰል ፎቶዎችን እየተከታተለች ሪፖርት ታደርጋለች።
እንደ ጆዋና ባሉ መሰል ሰዎች ተከታታይ ጥረት ምክንያት ይህ ታዋቂ ቻናል በስተመጨረሻም እንዲዘጋ ሆኗል። ነገር ግን አንደኛው ሲዘጋ ሌላ ተመሳሳይ ግሩፕ ይፈጠራል። ተመሳሳይ ሰዎችም ይከተሉታል።
“አንዳንድ ጊዜ በጣም ተስፋ ያስቆርጣል። ምክንያቱም እኛ ይሄን ሁሉ ነገር አድርገን አንዱን ስናስዘጋ ሌሎች አዳዲስ ይፈጠራሉ። መጨረሻ ያለው አይመስልም” ትላለች ጆዋና።
ቴሌግራም ከቢቢሲ ለቀረበለት የቃለ መጠይቅ ሀሳብ ሳይስማማ ቀርቷል። በምላሹም መሰል እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ተጠቃሚዎች ላይ የተመሰረት የመከላከል ሥራ እንደሚያከናውን ገልጿል።
ቴሌግራም በሁሉም የዓለማችን ከፍል የሚገኙ ተጠቃሚዎችን መሳብ መጀመሩን ተከትሎ መሰል ቡድኖች እና ቻናሎችን ለመቆጣጠር ምን አይነት እርምጃዎችን እንደሚወስድ የሚታይ ይሆናል።
የእርቃን ፎቶዎቻቸው ለሺዎች እንዲጋራ የተደረገባቸው ሴቶች ግን ሕይወታቸው ተመሰቃቅሎና በፍርሀት ውስጥ እየኖሩ ነው። ነገሮች ግን በቅርቡ መፍትሄ የሚያገኙ አይመስሉም።