17 የካቲት 2022, 10:44 EAT

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ሁለት አምቡላንሶች እንደተወሰዱበት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ገለጸ።
የማህበሩ የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ እና የግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን አሊ በቄለም ወለጋ ቅርንጫፍ ንብረት የሆኑና ማህበሩ ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚጠቀምባቸው ሁለት አምቡላንሶች በስራ ላይ እያሉ መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አምቡላንሶቹ ለሰብዓዊ አገልግሎት እየተንቀሳቀሱ ነበር ያሉት ዶ/ር ሰለሞን ማህበሩ በማያውቀውና በግዳጅ መወሰዳቸውን ያስረዳሉ።
ዶክተር ሰለሞን የአምቡላንሶቹ አሽከርካሪዎች ደህንነት እንደተጠበቀ መሆኑን ገልጸው፤ አምቡላንሶቹ በማን እንደተወሰዱ? ለምን እንደተወሰዱ ማህበሩ ዝርዝር መረጃ እንደሌለውና በቀጣይም አስፈላጊ በሆነ መልኩ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
በዞኑ ማህበረሰብ ድጋፍ ለሰብዓዊ አገልግሎት ላይ የዋሉ አስራ አንድ አምቡላንሶች ሲኖሩ ሁለቱ ባልታወቀ ሁኔታ መወሰዳቸውን ተከትሎም ሌሎች ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ።
ድርጊቱ ኢትዮጵያ የፈረመችውን አለም አቀፍ የጄኔቫ ኮንቬንሽን የሚጻረርና ከማህበሩ ዓላማ ውጭ መሆኑን ማህበሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሮ የተጠቀሱት ታርጋ ቁጥሮች የያዙ አምቡላንሶቹ እንዲመለሱለት ጠይቋል።
- ቀይ መስቀል በሰሜን ኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ እጥረት አሳስቦኛል አለ
- ከአምስት ወራት በኋላ የሕክምና መገልገያዎች ዛሬ ትግራይ መድረሳቸውን ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ
- ተመድ በትግራይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች እንዳሳሰቡት ገለጸ
በተጨማሪም አምቡላንሶችን በሃይል መውሰድ፣ በሃይል መጠቀምም ሆነ በአላስፈላጊ ሁኔታዎች ላይ ማዋል ከጄኔቫ ኮንቬንሽን ክልከላ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ ወንጀል መሆኑንና እስከ አምስት አመት የሚያሳስር ድርጊት ሆኖም መደንገጉን ይናገራሉ።
ሆኖም ቀይ መስቀል ጦርነትና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች እንዲህ አይነት ድርጊቶች ብዙ ጊዜ እንደሚያጋጥሙት ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል።
የአምቡላንሶች መቆረጥ፣ መሰወር፣ በማይታወቁ ኃይሎች መወሰድ በተለያዩ ጊዜዎች እንደሚያጋጥሙ የሚናገሩት ዶክተር ሰለሞን በዚያው አካባቢ ከዚህ ቀደም ሁለት አምቡላንሶች መቃጠላቸውን አስታውሰዋል።
ማህበሩ በ86 አመት ታሪኩ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አምቡላንሶችና በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ በአየር ጥቃት የተደበደቡበትን ጠቅሰው በጦርነትና በግጭቶች ብዙ ጉዳት ይደርሳል ይላሉ።
በባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ በትግራይ በተከሰተው ጦርነትም በሁመራና ጭልጋ አካባቢ አምቡላንሶች በጥይት የተመቱ ሲሆን በጎ ፈቃደኞች ላይ ግን አደጋ አልደረሰም ብለዋል።
በትግራይ ያሉ ከ200 በላይ አምቡላንሶቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁና አንዳንድ ጊዜም በአንዳንድ አካባቢዎች አምቡላንሶች ጠፍተው የሚገኙበት አጋጣሚም እንዳለም ዶክተር ሰለሞን አክለዋል።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎና ጎንደር አምቡላንሶች ጠፍተው የተገኙበትን ሁኔታንም አንስተዋል።
ዶክተር ሰለሞን በዚህም በአንድ አመት ከሶስት ወር ውስጥ አምቡላንሶቻቸው ለአደጋ የተጋለጡበትና የተሰወሩበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸው ይህንንም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የቀይ መስቀል አመሰራረቱ በጦርነትና በግጭት እርዳታ መስጠት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የማህበሩ በጎ ፈቃደኞች የቆሰሉትን ለማንሳትና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት ሲሉ ለአደጋ የሚጋለጡበት ጊዜ አለ ይላሉ- ዶክተር ሰለሞን።
በተለይም ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለወራት ሰራተኞቻቸውን የማያገኙባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ “ትግራይ ውስጥ ያሉ ወደ አምስት መቶ የሚደርሱ በጎ ፈቃደኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚሰሩት” ብለዋል።
“ጦርነት ሲመጣ ቀይ መስቀልን ጨምሮ ሁሉም ወገን ነው የሚጎዳው።” ይላሉ።
ሆኖም ” ማህበሩ ይህን ሰብዓዊ ስራ መሥራት ከጀመረ ሁለት መቶ አመት ሊደርስ ነው። ዋናው ትኩረታችን የተጎዳን ማንሳት፣ የተራበን ማብላት፣ ከቤተሰብ ጋር ማገናኘት ስለሆነ በሚደርሱብን ችግሮች ላይ አናተኩርም” ብለዋል።
ምንም እንኳን ተቋሙ በጦርነትና ግጭት አካባቢዎች ዋነኛ የሰብዓዊ እርዳታ ቢሰጥም በግጭቶች መካከል ካልተፈቀደ የማይገቡባቸው ሁኔታዎች እንዳሉና ህጎችና ደንቦችን አክብረው እንደሚሰሩ ያስረዳሉ።
በእንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች የጄኔቫ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ለምሳሌ የመከላከያ ሰራዊት ራሱ አርማውን ተጠቅሞ ታካሚዎችን ያንቀሳቅሳል።
አለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ በአለም ላይ 192 በሚሆኑ አገራት ውስጥ በነፃ፣ ገለልተኛና በማያዳላ መልኩ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው።
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ ማህበሩ “ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ክፍፍሎችን መሰረት ያላደረገ ሰብዓዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ ያደርጋል”።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርም ይህንኑ መርህ ተከትሎ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ነው የሚሰራው የሚሉት ዶክተር ሰለሞን ጦርነት ህግ ስለሌለው መሃል ላይ የመያዝ ሁኔታም እንደሚያጋጥም ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስል ማህበር 45 ሺህ የሚሆኑ የሰለጠኑ በጎ ፈቃደኞች፣ በአጠቃላይ 200 ሺህ በጎ ፈቃደኞችና፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት።
ዶክተር ሰለሞን እንደሚያስረዱት የቀይ መስቀል አርማ ያላቸው አምቡላንሶችም ሆነ ሰራተኞቻቸውና በጎ ፈቃደኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችለው የጄኔቫ ኮንቬንሽን አለ።